ቀጥታ፡

ህብረተሰቡ የኮቪድ-19 ክትባትን በመውሰድ የበሽታውን ስርጭት እንዲገታ የሕክምና ባለሙያዎች ማኅበር ጥሪ አቀረበ

ታህሳስ 20/2015(ኢዜአ) ህብረተሰቡ የኮቪድ-19 ክትባትን በአግባቡ በመውሰድ ሥርጭቱን መግታት እንዳለበት የኢትዮጵያ የሕክምና ባለሙያዎች ማኅበር ጥሪ አቀረበ።

ማኅበሩ የኮቪድ-19 የክትባት ሁኔታና አጠቃቀም ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ አካሂዷል።

እየታየ ያለው ጉንፋን መሰል ወረርሽኝ በአብዛኛው የኮቪድ-19 ምልክት እያሳየ መሆኑን የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በቅርቡ መናገሩ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ የሕክምና ባለሙያዎች ማኅበር ዳይሬክተር ትዕግስት መኮንን እንደገለጹት፤ ኮቪድ-19 በዓለም አቀፍ ደረጃ መከሰቱን ተከትሎ በርካታ ሰዎች በወረርሽኙ ሳቢያ ለውስብስብ የጤና ጉዳቶችና ለሞት መዳረጋቸውን አስታውሰዋል።

በተጨማሪም አገራት ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ተጋላጭ እንደነበሩ ገልጸው፤ ችግሩ በታዳጊ አገራት ላይ በእጅጉ የከፋ እንደነበርም ተናግረዋል።

ይህንን ተከትሎ ወረርሽኙን ለመግታት በተለያዩ አገራት የተመረቱ የተለያየ ዓይነት የኮቪድ-19 ክትባቶች ተደራሽ መደረጋቸውን አንስተው ኢትዮጵያም የወረረሽኙን ሥርጭት ለመግታትና የዜጎችን በኮቪድ የመያዝ ምጣኔን ለመቀነስ ክትባቶቹን በግዥና በእርዳታ በማስገባት ለማኅበረሰቡ ተደራሽ እያደረገች መሆኑን ጠቁመዋል።

በክትባቱ ዙሪያ ያለው የማኅበረሰቡ ግንዛቤ ዝቅተኛ መሆኑ ክትባቱ በሚፈለገው መልኩ ተግባር ላይ እንዳልዋለና በአሁኑ ወቅትም በርካታ የኮቪድ-19 ክትባቶች የመጠቀሚያ ጊዜያቸው በማለፉ ለብክነት መዳረጉን ነው ዳይሬክተሯ የጠቆሙት።

በተለይም ወረርሽኙ ዓይነቱን እየቀያየረ የመከሰት ዕድሉ ሰፊ መሆኑን አብራርተው፤ ክትባቱን ባልተከተቡ ዜጎች ላይ ደግሞ የመባባስ ዕድሉ ሰፊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

በመሆኑም ሕብረተሰቡ በአገሪቱ ክትባቱ በበቂ ሁኔታ መኖሩን ተገንዝቦ በአግባቡ ሊከተብ እንደሚገባ መልዕክት አሰተላልፈዋል።

በፕሮጀክት ሆፕ ኢትዮጵያ የኮቪድ ክትባት አማካሪ የሆኑት ኃይሌ ካሳሁን፤  የኮቪድ-19 ክትባት አስፈላጊነትና አጠቃቀምን በሚመለከት ገለጻ ሲያደርጉ ክትባቱ 80 በመቶ በኮቪድ የመያዝ አቅምን በማጎልበት በሽታ የመከላከል አቅም እንዲኖር ያግዛል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ አራት ዓይነት ደረጃቸውን የጠበቁ የኮቪድ ክትባቶች እንዳሉ ጠቁመው፤ በኢትዮጵያ አራቱም ክትባቶች እየተሰጡ መሆኑን አስረድተዋል።

ይሁን እንጂ ስለ ክትባቱ በቂ ግንዛቤ ኖሯቸው የሚከተቡ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጥቂት መሆናቸውን  ጠቅሰው፤ የክትባቱ ተደራሽነት ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ መሆኑን አመልክተዋል።

በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ዳይሬክተር ስንዱ መኩሪያ በበኩላቸው፤ በአገሪቱ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ የኮቪድ-19 ክትባት በሁሉም የጤና ተቋማት፣ ሕዝብ በብዛት በሚሰበሰብባቸው አካባቢዎች፣ በተቋማትና በትምህርት ቤቶች ተደራሽ ሲደረግ እንደነበር አስታውሰዋል።

በአገር አቀፍ ደረጃም ሦስት ጊዜ የዘመቻ ክትባት ሲካሄድ በአዲስ አበባ ለአራት ጊዜ መካሄዱን ገልጸው፤ አሁንም የኮቪድ ክትባት ዘመቻው እየተካሄደ ነው ብለዋል።

በመሆኑም ክትባቱን ተደራሽ ከማድረግ ጎን ለጎን ስለ ክትባቱ ያለውን ግንዛቤ ማዳበርና ማስገንዘብ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑንም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም