ቦሩ ሜዳ ጠቅላላ ሆስፒታል ለ3 ሺህ 200 ሰዎች የዓይን ሞራ ግርዶሽ ህክምና ሰጠ - ኢዜአ አማርኛ
ቦሩ ሜዳ ጠቅላላ ሆስፒታል ለ3 ሺህ 200 ሰዎች የዓይን ሞራ ግርዶሽ ህክምና ሰጠ
ደሴ (ኢዜአ) ታህሳስ 20/2015 በደሴ ከተማ የቦሩ ሜዳ ጠቅላላ ሆስፒታል በዓይን ሞራ ግርዶሽ ለታመሙ 3 ሺህ 200 ሰዎች ነጻ የዓይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ህክምና መስጠቱን አስታወቀ፡፡
የሆስፒታሉ ስራ አስኪያጅ አቶ ሲሳይ ተበጀ ለኢዜአ እንደገለጹት ህክምናው የተሰጠው ከታህሳስ 3 እስከ 19 ቀን 2015ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ በተካሄደ ዘመቻ ነው፡፡
በዘመቻው 6 የዓይን ህክምና ስፔሻሊስት ዶክተሮችን ጨምሮ 24 የውጭና የሀገር ውስጥ የዓይን ሐኪሞች የተሳተፉ ሲሆን በዚህም 3 ሺህ 200 ሰዎችን ከዓይነ ስውርነት መታደግ መቻሉን ገልፀዋል።
በዘመቻው ደሴና ኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደሮችን ጨምሮ ከደቡብ ወሎ፣ ሰሜን ወሎ፣ ኦሮሞ ብሔረሰብ ዞንና አፋር ክልል በከፊል በበሽታው ተይዘው የነበሩ ሰዎች ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።
እንደ ስራ አስኪያጁ ገለጻ የታካሚዎች የትራንስፖርት ወጪን ጨምሮ ሌሎች ወጪዎችም በመንግስት መሸፈኑ በርካታ ሰዎች ህክምናውን እንዲያገኙ እድል ፈጥሯል ብለዋል፡፡
በሆስፒታሉ የዓይን ህክምና ክፍል ሃላፊ አቶ እንዳልክ ያረጋል በበኩላቸው በሽታው አብዛኛውን ጊዜ ከዕድሜ መግፋት ጋር ተያይዞ እንደሚከሰት ገልጸው በሽታው በወቅቱ ከታከመ መዳን እንደሚችል ጠቁመው፤ ካልታከመ ግን ዓይነ ስውርነትን ያስከትላል ብለዋል።
በዘመቻው በተደረገው ርብርብ የበርካቶችን ብርሃን መመለስ ተችሏል ያሉት ሃላፊው፤ ህብርተሰቡ በሽታው እንደተከሰተ ወደ ህክምና ተቋማት በመሄድ በወቅቱ መታከም እንደሚገባው አመልክተዋል።
ከታካሚዎቹ መካከል የአምባሰል ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ተስፋሁን ሰይድ እንዳሉት በዓይናቸው መታመም ምክንያት ከግብርና ስራ ውጭ ከመሆናቸውም በላይ በሰዎች እርዳታ ይንቀሳቀሱ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
በሆስፒታሉ ባገኙት ህክምና የዓይን ብርሃናቸው በመመለሱ እንደቀደመው ሁሉ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ሆነው የግብርና ስራቸውን እንዲከውኑ እድል የፈጠረላቸው መሆኑን ገልፀዋል።
ህክምናውን በነጻ ማግኘታቸውና ወጪያቸውም በመንግስት በመሸፈኑ አመስግነዋል፡፡
በደሴ ከተማ አስተዳደር የሚገኘው የቦሩ ሜዳ ጠቅላላ ሆስፒታል የአሁኑን ጨምሮ ባለፉት አራት ዓመታት ከ8 ሺህ ለሚበልጡ ሰዎች የዓይን ሕክምና መስጠት እንደቻለ መረጃዎች ያሳያሉ።