ቀጥታ፡

በትግራይ ክልል አስቸኳይ የሰብዓዊ ድጋፍ እየቀረበ መሆኑንና መሰረታዊ አገልግሎቶች መጀመራቸውን እንዳረጋገጡ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ ገለፁ

በአፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ የተመራ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ልዑክ በመቀሌ ያደረገው ጉብኝትም የመንግስትን ቁርጠኝነት ያረጋገጠ ነው ብለዋል

የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ በትግራይ ክልል አስቸኳይ የሰብዓዊ ድጋፍ በስፋት እየቀረበ ሲሆን መሰረታዊ አገልግሎቶችም መጀመራቸውን በአፍሪካ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልእክተኛ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ ገለጹ።

የህብረቱ ልዩ መልእክተኛ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆና የቀድሞ የኬኒያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ፤ በመንግስትና ህወሓት መካከል የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ አፈፃፀሙን ለመመልከት በመቀሌ ተገኝተዋል።

በትግራይ መሰረታዊ አገልግሎቶች ዳግም እንዲጀመሩና ሰብአዊ ድጋፍ ተደራሽ በማድረግ የመንግስትን ቁርጠኝነት ያደነቁት ልዩ መልእክተኛው የመንግስትና የህወሓት አመራሮችም ለሰላም ስምምነቱ ላደረጉት ቀና ተግባር አመስግነዋል።

በሰሜን ኢትዮጵያ ሰብዓዊ ድጋፍ ያለ ገደብ ማቅረብ፣ መሰረታዊ አገልግሎቶችን መልሶ ማስጀመርና ዘላቂ ሰላም ማስፈን የሰላም ስምምነቱ አካል እንደነበርም አስታውሰው ስምምነቱን ተከትሎ መንግስት በገባው ቃል መሰረት ሁሉንም ነገሮች ተፈፃሚ በማድረግ ላይ በመሆኑ አመስግነዋል።

በትግራይ ኤሌክትሪክ፣ ባንክ፣ ቴሌኮሙኒኬሽን፣ መንገድ፣ እንዲሁም ሌሎች መሰረታዊ አገልግሎቶች በአጭር ጊዜ አገልግሎት መስጠት መጀመራቸው የሚደነቅ መሆኑንም ገልጸዋል።

የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ መንግስት የሚታዩ አወንታዊ ርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑን ጠቅሰው በአፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ የተመራ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ልዑክ በመቀሌ ያደረገው ጉብኝትም የመንግስትን ቁርጠኝነት ያረጋገጠ ነው ብለዋል።

የአፍሪካ ህብረት፣ የኢትዮጵያ ህዝብ፣ የሁለቱ ወገኖች ሲቪልና ወታደራዊ አመራሮች ለዚህ ውጤት መምጣት ድርሻው የጎላ በመሆኑ ምስጋና ይገባቸዋልም ነው ያሉት ልዩ መልእክተኛው።

የቀድሞው የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ፤ ሁሉም የትራንስፖርት መተላለፊያዎች ለአስቸኳይ ሰብዓዊ እርዳታና መሰረታዊ አገልግሎቶች ክፍት መደረጋቸውን አረጋግጠናል ብለዋል።

በትግራይ ክልል የሰብዓዊ እርዳታን ጨምሮ የአየር ትራንስፖርት፣ መንገድ፣ ባንኮች፣ የኤሌክትሪክና ሌሎችም አገልግሎቶች ዳግም ስራ መጀመራቸው የሚደነቅ መሆኑንም ገልጸዋል።

"ለዚህ ውጤት የሁለቱ ወገኖች አመራሮች ምስጋና ይገባቸዋል፣ እኛም ትብብራችንን አጠናክረን እንቀጥላለን" ሲሉ ተናግረው የሰላም ስምምነቱ አፈፃፀም ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ መስጠት እንደሚቻል ሁነኛ ማሳያ መሆኑንም ገልጸዋል።

የፍትህ ሚኒስትሩ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ በበኩላቸው፤ መንግስት የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ በገባው ቃል መሰረት ሁሉንም ነገሮች ተፈፃሚ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በቀጣይም በሁሉም መስክ በቁርጠኝነት የሚሰራ መሆኑን አረጋግጠው የሰላም ስምምነቱ አፈፃፀም ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ መስጠት እንደሚቻል ማሳያ ነው ብለዋል።

የህወሓት ከፍተኛ አመራር አቶ ጌታቸው ረዳ፤ በትግራይ የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦቱን ጨምሮ የሰላም ስምምነቱ በሁለቱም ወገኖች ዘንድ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም