ቀጥታ፡

የኢንዱስትሪ ዘርፉ በአገር ምጣኔ ሃብት ዕድገት የድርሻውን እንዲወጣ እየተሰራ የሚገኘው የተቀናጀ ስራ ውጤት እያመጣ ነው--የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበ

ድሬዳዋ (ኢዜአ) ታህሳስ 20/2015 የኢንዱስትሪ ዘርፉ በአገር ምጣኔ ሃብት ዕድገት የድርሻውን እንዲወጣ እየተሰራ የሚገኘው የተቀናጀ ስራ ውጤት እያመጣ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል ገለጹ።

የኢንዱስትሪው ዘርፍ በአገር ምጣኔ ሃብት ዕድገት ላይ የድርሻውን እንዲወጣ በአገር ደረጃ የተጀመረውን ዘላቂ ሰላም የማፅናት ስራ ላይ ሁሉም መረባረብ አለበትም ብለዋል።

"የኢትዮጵያ ታምርት" የኢንዱስትሪ ንቅናቄ ዛሬ በድሬደዋ ተካሂዷል።

በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል አገር አቀፍ ለውጡን ተከትሎ በተካሄዱ የሪፎርም ስራዎች በማህበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ዕድገት ላይ አበረታች ውጤቶች ተመዝግቧል።

በግብርናው፣ በቱሪዝም፣ በቴክኖሎጂው፣ በመሠረተ ልማቶች፣ በኢንዱስትሪው እና ሌሎች መስኮች የተገኙ ለውጦችን በመጥቀስ።

በተለይ በኢትዮጵያ ታምርት የኢንዱስትሪ ዘርፍ የተጀመረው አገር አቀፍ ንቅናቄ በመላው አገሪቱ የሚገኙ ነባርና አዳዲስ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች በሙሉ አቅማቸው እንዲያመርቱ ዕድል ፈጥሯል ሲሉም ገልጸዋል።

ከዚህ በተጨማሪ የተዘጉ ኢንዱስትሪዎች ዳግም ወደ ስራ እንዲገቡ በማድረግ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት እና የተሻለ የስራ ዕድል በመፍጠር ተጨባጭ ውጤቶች መመዝገብ መቻሉንም ተናግረዋል።

በድሬዳዋ እየተካሄደ የሚገኘው ንቅናቄ፤ በተመቻቹ ትላልቅ ሼዶች እና የመሠረተ ልማት አቅርቦቶች ጥሩ ውጤቶች በዘርፉ እንዲመዘገብ ማስቻላቸውን ተናግረው በዘርፉ እየተፈጠረ የሚገኘው የስራ ዕድል ማደግ እንዳለበት ነው ያስገነዘቡት።

የፌዴራል መንግስት ድሬደዋን የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ የተቀናጀ ስራ እየሰራ መሆኑንም አክለዋለ።

ለዚህም ድሬዳዋ ያላት ስትራቴጂካዊ አቀማመጥ፣ የኢንደስትሪ ግብአቶች፤ የየብስ እና የአየር ትራንስፖርት መሠረተ ልማቶቿ ለሚፈለገው ዕድገት እንዲውሉ እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠል አለባቸውም ብለዋል።

በኢትዮጵያ ታምርት የኢንዱስትሪ ንቅናቄው ሆነ በአገር ደረጃ እየተመዘገቡ የሚገኙ ጅምር ውጤቶች በስኬት ለማስቀጠል እና ውስብስብ የምጣኔ ሃብት ችግሮችን ለመፍታት እንደ አገር የተጀመረው ዘላቂ ሰላም የማስፈን ስራ ላይ ሁሉም ተቀናጅቶ መስራት እንዳለበት ጠቁመዋል።

የምጣኔ ሃብት ዕድገት እና ሰላም የአንድ ሣንቲም ሁለት ገፅታዎች ናቸው ያሉት ሚኒስትሩ የውጭ ባለሃብቶች በተመቻቸላቸው መስክ መዋዕለ ነዋያቸውን በስራ ላይ እንዲያውሉ ለማድረግ ጥሪ አቅርበዋል።

ለዚህ ደግሞ ከሰላም ባሻገር በጥናት የተደገፈ ፈጣን እና ቀልጣፋ አገልግሎት፣ የተሟላ መሠረተ ልማት ማቅረብ ላይ በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር በበኩላቸው በፌዴራል መንግስት ከፍተኛ ዕገዛ ድሬዳዋ የአገሪቱ የኢንዱስትሪ ማዕከልነቷን የሚያረጋግጡ ስራዎች እየሠሩ መሆናቸውን ገልፀዋል።

በኢትዮጵያ ታምርት የኢንዱስትሪ ንቅናቄ እየተመዘገቡ የሚገኙት ውጤቶች የዚሁ ማሳያ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

የተገኙ ለውጦችን በላቀ ደረጃ በማሳደግ የምጣኔ ሃብት ምሶሶ የኢንዱስትሪ ዘርፍ እንዲሆን የተቀመጠውን አቅጣጫ ለማሳካት ርብርቡ ይጠናከራል ብለዋል።

ድሬዳዋ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ያላትን ልምዶች፣ መሠረተ ልማቷች፣ አሁን የተፈጠረው ነፃ የንግድ ቀጠና በዘርፉ የሚፈለገውን ውጤቶች ለማስመዝገብ ያስችላታል ሲሉ የገለጹት ደግሞ የአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ እና የድሬዳዋ የንግድ ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀርቢ ቡህ ናቸው።

ዘንድሮ አስተዳደሩ በመሰረተው የኢንዱስትሪ መንደር ወደ ስራ በገቡ ከቀላል እስከ ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ከ12,600 በላይ ሰዎች ቋሚ እና ጊዚያዊ የስራ ዕድል መፈጠሩን የቢሮ ሀላፊው ጨምረው ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም