ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የሰሜኑን ችግር በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እያደረገች ያለው ጥረት የበርካቶችን ክብርና አድናቆት እያስገኘ ነው- በእንግሊዝ የኢትዮጵያ አምባሳደር

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 20/2015 ኢትዮጵያ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የነበረውን ችግር በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እያደረገች ያለው ጥረት የበርካቶችን ክብርና አድናቆት እያስገኘ መሆኑን በእንግሊዝ የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈሪ መለሰ ገለጹ።

ኢትዮጵያና እንግሊዝ የቆየ ዲፕሎማሲያዊ የትብብር ግንኙነት በተጠናከረ መልኩ የሚቀጥል መሆኑንም ተናግረዋል።

በእንግሊዝ የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈሪ መለሰ፤ በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረው ችግር በሰላማዊ ውይይት እልባት እያገኘበት ያለውን ሂደትና አጠቃላይ በዲፕሎማሲው መስክ የሚኖረውን ፋይዳ በተመለከተ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

በአፍሪካ ሕብረት አመቻችነት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በተደረሰው የሰላም ስምምነት መሰረት በመንግሥት በኩል ተፈጻሚ እንዲሆኑ ንግግር የተደረገባቸው ጉዳዮች በሁሉም መስክ ተፈጻሚ በመሆን ላይ ናቸው ብለዋል።

በዚህም የስልክ፣ የመብራት እና  የባንክ አገልግሎት በተሳለጠና በተፋጠነ መልኩ በመሰጠት ላይ ሲሆን፤ የምግብና የመድኃኒት አቅርቦትም በስፋት ተደራሽ መደረጉ የመንግሥትን ቁርጠኝነት በተግባር ያረጋገጠ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የነበረውን ችግር በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እያደረገች ያለው ጥረት ከውጭም ከውስጥም የበርካቶችን ክብርና አድናቆት እያስገኘ ነው ብለዋል አምባሳደር ተፈሪ።

የኢትዮጵያ የውስጥ ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም አንድነቷ እየተጠናከረ መሄዱ ለዲፕሎማሲውም ጥሩ መሠረት ስለመሆኑ አብራርተዋል።

ኢትዮጵያና እንግሊዝ ለረዥም ዘመናት የቆየ ታሪካዊ ግንኙነት ያላቸው አገሮች መሆናቸውን የጠቀሱት አምባሳደር ተፈሪ፤ የጋራ ተጠቃሚነትን መሠረት ባደረገ መልኩ የትብብር ግንኙነቱ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት በተመለከተ እንግሊዝ ድጋፏን መግለጿን አስታውሰው፤

ሀገራቱ በተለይም በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በቱሪዝምና በቴክኖሎጂ ሽግግር በጋራ የሚሰሩ መሆኑን ነው የተናገሩት።

የኢትዮጵያና እንግሊዝ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የተጀመረው በ1841 ዓ.ም ሲሆን ከአፍሪካ አገሮች መካከል በለንደን ኤምባሲ በመክፈት ኢትዮጵያ ቀዳሚ መሆኗንም መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም