ቀጥታ፡

የሀገር ውስጥና የውጭ አገር የስራ ስምሪት በቴክኖሎጂ ለመምራት የሚያስችል ሶፍት ዌር እየበለፀገ ነው

አዳማ ታህሳስ 20/2015(ኢዜአ) የሀገር ውስጥና የውጭ አገር የስራ ስምሪት በቴክኖሎጂ ለመምራት የሚያስችል ሶፍት ዌር እያበለፀጉ መሆኑን የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ገለፀ።

ሚኒስቴሩ ከሁሉም ክልሎችና ሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበትና በሰው ሃይል መረጃ አያያዝና የስራ ስምሪት ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ በአዳማ በማካሄድ ላይ ይገኛል።

የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ አሰግድ ጌታቸው በሀገሪቷ ያለውን የስራ አጥ መጠን ለማወቅና የገበያ አማራጮችን ማቀፍ የሚችል ሶፍት ዌር እየበለፀገ ነው ብለዋል።

የውጭ ሀገር የስራ ስምሪት፣ የአሰሪና ሰራተኛ ዘርፍ ስትራቴጅና ፖሊስ ቀረፃም ከዚሁ ጎን ለጎን እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።

የስራ ፍሰትና የአንድ ማእከል አገልግሎት ግንባታን ተከትሎ በርካታ የውጭ  አገር የስራ ስምሪት እንዲኖር በሚያስችል መልኩ በበየነ መረብ አገልግሎት የሚያገኙበት አሰራር በመዘርጋት የኤጄንሲዎች ምዝገባ እየተከናወነ መሆኑን ነው የተናገሩት።

የስራ ፍሰት፣ የገበያና የሙያ መረጃ፣ የስራ አጥ መጠን መመዝገቢያና አማራጭ የስራ እድሎች እንዲሁም ዩኒቨርሲቲዎችና የስልጠና ተቋማት ሙያና ገበያን የሚያገናኝ ትምህርትና ስልጠና እንዲሰጡ የሚያግዝ ሶፍት ዌር መሆኑንም አመልክተዋል።

የመድረኩ ዓላማም በዘርፉ ያሉ ባለድርሻ አካላት በሚያደርጉት ውይይት ግብዓት ለማሰባሰብ መሆኑን ተናግረዋል።

ወደ ውጭ የሚሰማረው የሰው ሃይል በተለይም ከዝቅተኛ እስከ ከፍተኛ ባለሙያ የውጭ የስራ ስምሪት እንዲኖር የገበያ መዳረሻዎች ጥናት እንደሚደረግና የትኛው ሙያ በየትኛው ሀገር ይፈለጋል የሚለውን የመለየት ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

የመንግስትና የግል የስልጠና ተቋማት የሀገር ውስጥና የውጭ የስራ ገበያ ፍላጎትን መሰረት አድርገው ትምህርትና ስልጠና እንዲሰጡና ተቋማቱ ከማሰልጠን ጀምረው የሙያ ምዘና ብቃት እንዲያረጋግጡ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በሚኒስቴሩ የውጭ ሀገር የስራ ስምሪት መሪ ስራ አስፈፃሚ ወይዘሮ እምዬ ብተው በበኩላቸው የውጭ ሀገር ስራ ስምሪትን ቀልጣፋና ከብልሹ አሰራር የፀዳ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም ወደ ውጭ የሚሄዱ ዜጎችን መብትና ክብር ለማስጠበቅ የሚያስችል አሰራሮች እየተዘረጉ መሆኑን ገልጸው፤ ወደ ውጭ ለስራ የሚልኩ ኤጄንሲዎች ካፒታል፣ ፍቃድና የሚሰጡት ስልጠና በቴክኖሎጂና በአሻራ ተመዝግበው እንዲያዙ ስርዓት እየተዘረጋ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም