ቀጥታ፡

40ኛው የጃንሜዳ ኢንተርናሽናል አገር አቋራጭ ውድድር እሑድ በሱሉልታ ከተማ ይካሄዳል

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 20/2015 40ኛው የጃንሜዳ ኢንተርናሽናል አገር አቋራጭ ውድድር እሑድ በሱሉልታ ከተማ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ገለጸ።

የፌዴሬሽኑ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት አትሌት ገዛኸኝ አበራ፤ 40ኛው የጃንሜዳ ኢንተርናሽናል አገር አቋራጭ ውድድር እሑድ በሱሉልታ ከተማ እንደሚካሄድ ገልጸው በውድድሩ ከ1 ሺህ 29 በላይ አትሌቶች ይካፈላሉ ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል።

ውድድሩ ከጃንሜዳ ወደ ሱሉልታ የቦታ ለውጥ የተደረገው ጃንሜዳ ኮቪድ-19 በገባበት ወቅት የአትክልት መሸጫ ሥፍራ ሆኖ ሲያገለግል በመቆየቱ ለውድድር አመቺ ባለመሆኑ እንደሆነ ገልጸዋል።

በተለይም ጃንሜዳ ለመገበያያ እንዲያመች ድንጋይና ጠጠር ተደልድሎበት በመቆየቱ አሁንም ላይ ለውድድር አመቺ አለመሆኑን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚደንቱ ጠቁመዋል።

የፌዴሬሽኑ የውድድርና ተሳትፎ የሥራ ሂደት መሪ አስፋው ዳኜ፤ ውድድሩ በ10 ኪሎ ሜትር በአዋቂ ወንዶችና ሴቶች፣ በ8 ኪሎ ሜትር በወጣት ወንዶች፣ በ6 ኪሎ ሜትር በወጣት ሴቶች፣ በ8 ኪሎ ሜትር ድብልቅ ሪሌና በአንጋፋ አትሌቶች መካከል የሚካሄድ መሆኑን ገልጸዋል።

በውድድሩ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃ ይዘው ለሚያጠናቅቁ ተወዳዳሪዎች የወርቅ፣ የብርና የነሐስ ሜዳሊያ ይሰጣቸዋል ተብሏል።

በአዋቂ ወንዶችና ሴቶች ውድድር ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ለሚያጠናቅቁ ለእያንዳንዳቸው እንደ የደረጃቸው ከ50ሺህ ብር እስከ 14 ሺህ ብር የገንዘብ ሽልማት ስለመዘጋጀቱም ተጠቅሷል።

በወጣት ወንዶችና ሴቶችም ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ሆነው ለሚያጠናቅቁም ለእያንዳንዳቸው እንደ የደረጃቸው ከ40 ሺህ እስከ 10 ሺህ ብር ሽልማት መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።

በድብልቅ ሪሌ እና ለአንጋፋ አትሌቶችም የገንዘብ ሽልማት መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።

በዚህ ሻምፒዮና አሸናፊ የሚሆኑ አትሌቶች በየካቲት ወር 2015 ዓ.ም በአውስትራሊያ በሚካሄደው 44ኛው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ላይ እንደሚካፈሉም ተገልጿል።

በሩጫው እንዲሳተፉ ጥሪ ከተደረገላቸው አገሮች መካከል የሱዳን አትሌቶች እንደሚሳተፉ ማረጋገጫ መስጠታቸው ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም