በሀገሪቷ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ሴቶች ግንባር ቀደም ሚና እንዲወጡ ተጠየቀ

25

አዳማ (ኢዜአ )ታህሳስ 20/2015 በሀገሪቷ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ሴቶች ግንባር ቀደም ሚና እንዲወጡ ተጠየቀ።

በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን እየተደረገ ባለው ሀገራዊ ጥረት ውስጥ ሴቶች የድርሻቸውን ማበርከት እንዲችሉ ሀገር አቀፍ የሴቶች የሰላም ኮንፈረንስ ንቅናቄ በአዳማ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አለሚቱ ዑሞድ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት በሰላም እጦት ምክንያት ለሚያጋጥሙ ችግሮች ሴቶች ተጋላጭነታቸው ከፍተኛ ነው ብለዋል።

ይህም በመሆኑ በሀገሪቷ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ሴቶች ግንባር ቀደም ሚና እንዲወጡ ጠይቀዋል።

በተጨማሪም ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት ውስጥ ሴቶች ንቁ ተሳታፊ መሆን እንደሚገባቸው ተናግረዋል።

''የኮንፈረንሱ ዋና ዓላማ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ በማጠናከር በሀገሪቷ ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ ህብረተሰቡን በማስተባበር ጭምር የድርሻችንን ለመወጣት ነው'' ብለዋል።

''ኮንፈረንሱ ተከትሎ ከፌዴራል ጀምሮ በየደረጃው የማህበረሰብ ንቅናቄ ይካሄዳል'' ያሉት ሚኒስትር ደኤታዋ ሴቶች ድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ሴቶች የሀገር ሰላም በመገንባት፣ በሽምግልና፣ በእርቅና በማረጋጋት ተግባራት ላይ በንቃት እንዲሳተፉ ቀጣይ የሚካሄደው ንቅንናቄ ምቹ እድሎችን የሚፈጥር መሆኑንም አመልክተዋል።

በኮንፈረንሱ ላይ ከሁሉም ክልሎችና የከተማ መስተዳድሮች የተወጣጡ የሴቶች አደረጃጀትና የሲቪክ ማህበራት ድርጅቶች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም