የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባለፉት 12 ወራት በዲጂታል የባንክ አገልግሎት ብቻ ከ1 ነጥብ 9 ትሪሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ልውውጥ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባለፉት 12 ወራት በዲጂታል የባንክ አገልግሎት ብቻ ከ1 ነጥብ 9 ትሪሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ልውውጥ አደረገ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 20/2015 የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባለፉት 12 ወራት በዲጂታል የባንክ አገልግሎት ብቻ ከ1 ነጥብ 9 ትሪሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ልውውጥ ማድረጉን የባንኩ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ ገልፀዋል።
የባንኩ ፕሬዝዳንት ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እያካሄደ የሚገኝውን የሪፎርም ስራ በተመለከተ ገለፃ አድርገዋል።
በዚህም የባንኩ የዲጂታል ባንክ አገልግሎት በሁሉም መመዘኛ የላቀ ደረጃ ላይ እየደረሰ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ባለፉት 12 ወራት ብቻ በዲጂታል የባንክ አገልግሎት ከ 1ነጥብ 9 ትሪሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ልውውጥ ማድረጉን አስታውቀዋል።
የገንዘብ ልውውጡ በሞባይል ባንኪንግ፣ ሲቢኢ ብር፣ ኢንተርኔት ባንኪንግ፣ ኤቲኤም እና በፖስ የባንኩ ዲጂታል አገልግሎቶች መሆኑን ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በዲጂታል ባንኪንግ ዘርፍ ፈር ቀዳጅ መሆኑን ያስታወሱት አቶ አቤ ሳኖ ለሌሎችም አርአያ መሆን የቻለ ባንክ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ባንኩ ቴክኖሎጂ ላይ መዋለንዋይ በማፍሰስ የራሱን አቅም በማጎልበት ቴክኖሎጂዎችን ለማበልጸግ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የባንኩን አሰራር ዘመናዊና ቀልጣፋ ለማድረግ ሁሉን አቀፍ የሪፎርም ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።