ፍቅር፣ ናፍቆትና ተስፋ የታየበት የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ዳግም ስራ መጀመር - አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን - ኢዜአ አማርኛ
ፍቅር፣ ናፍቆትና ተስፋ የታየበት የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ዳግም ስራ መጀመር - አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን
ታህሳስ 20/2015 (ኢዜአ) የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ መንግስት በገባው ቃል መሠረት በትግራይ ክልል ዳግም የተጀመረው መሰረታዊ አገልግሎቶች ፍቅር፣ ናፍቆትና ተስፋ የታየበት ነው ሲሉ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን የመንግሥት ከፍተኛ ልዑካን ወደ መቀሌ መሄድን ተከትሎ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ዳግም ስራ መጀመራቸውን የተመለከተ ሰፊ ዘገባ ሰርተዋል።
መንግስት በገባው ቃል መሰረት የተጀመሩ አገልግሎቶችን በተመለከተ የቱርኩ አናዶሉ በአፍሪካ አምዱ ባወጣው ዘገባ ከሁለት ዓመት ቆይታ በኋላ በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል የአገልግሎት ተቋማት ዳግም ስራ ጀመሩ ሲል አስነብቧል።
ከትላንት በስትያ ወደ መቀሌ ያቀኑትን ከፍተኛ የመንግስት ልዑካን ተከትሎ በክልሉ ለውጦች ታይተዋል ሲል ያመለከተው ዘገባው ከረቡዕ ጀምሮ ወደ መቀሌ ከተማ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ መጀመሩንና ሌሎችም አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ስራ መጀመራቸውን አስነብቧል።
የዳግም አገልግሎቱ ከአየር ትራንስፖርት በተጨማሪ፣ የቴሌኮም፣ የባንክ አገልግሎትና ሰብዓዊ ድጋፍንም ያካተተ ነው ሲል አትቷል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዳግም ወደ ትግራይ ክልል በረራ መጀመሩን አስመልከቶ ተነፋፍቀው የቆዩ ቤተሰቦች ፍቅራቸውን በእንባ ገለጹ ሲል የዘገበው ደግሞ ቲ አር ቲ ወርልድ ነው።
ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች ልዑክ ወደ መቀሌ ማቅናቱን ተከትሎ የአየር ትራንስፖርት፣ የቴሌኮም አገልግሎት፣ የባንክ አቅርቦት ዳግም መጀመራቸውንና የሰብአዊ ድጋፎችም እየቀረቡ እንደሚገኝ አስነብቧል።
ጦርነት አብቅቶ ፍቅር፣ ናፍቆትና ተስፋ የታየበት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ትግራይ ክልል ዳግም የጀመረው በረራ ሲል የዘገበው ደግሞ ሮይተርስ ነው።
በዚህም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዳግም የበረራ አገልግሎት መስጠቱ ከስምምነቱ ወዲህ ከታዩ ለውጦች መካከል ሰፊ ድርሻ አለው ነው ያለው።
በዘገባው የተካተቱ አስተያየት ሰጪዎችም ጦርነቱ አብቅቶ ከቤተሰቦቻቸው ጋር መገናኘታቸው እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል።
የኢፌዴሪ መንግስት በገባው ቃል መሰረት አየር መንገዱ ወደ መቀሌ መደበኛ በረራ መጀመርን ጨምሮ የመብራት እና የስልክ አገልግሎት እንዲጀመሩ እያደረገ መሆኑ ይታወቃል።