ኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅሟን ከማስጠበቅ ባለፈ ለአፍሪካ ጥቅምና ፍላጎት መከበር የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ ትቀጥላለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅሟን ከማስጠበቅ ባለፈ ለአፍሪካ ጥቅምና ፍላጎት መከበር የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ ትቀጥላለች
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 20/2015 ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው መስክ ብሄራዊ ጥቅሟን ከማስጠበቅ ባለፈ ለአፍሪካ ጥቅም መከበር የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ እንደምትቀጥል አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ ገለጹ።
በተለያዩ የዓለም አገራት ኢትዮጵያን የሚወክሉ አምባሳደሮች ከምንም በላይ የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም ማስጠበቅና ሁለንተናዊ የዲፕሎማሲ አቅሟን ከፍ ማድረግ መሆኑ ይታወቃል።
በተለዋዋጩ ዓለም ውስጥ የዲጅታል ዲፕሎማሲን ጨምሮ በመልከ ብዙ አማራጮች በየትም ቦታ ሆኖ የሚሰራበት አጋጣሚ በመፈጠሩ ዜጎችም ለአገራቸው ዲፕሎማት የሆኑበት የዲጅታል ዓለም ላይ ተደርሷል።
በመሆኑም ዲፕሎማቶች የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም፣ ክብርና መልካም ገጽታ ለማስጠበቅ ወቅቱን ያገናዘበ የዲፕሎማሲ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ፤ ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው መስክ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነች መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው መስክ ብሄራዊ ጥቅሟን ከማስጠበቅ ባለፈ ለአፍሪካ ጥቅምና ፍላጎት መከበር የላቀ ሚናዋን እየተወጣች መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ በተለይም የሰሜኑን ጦርነት ተከትሎ ባለፉት ሁለት ዓመታት በብዙ መልኩ ቢፈተንም በበርካታ ጥረቶች ችግሮቹ መታለፋቸውን አስታውስዋል።
በተለይም የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ በብዙ መልኩ የዲፕሎማሲው መስክ በጥሩ ሁኔታ ላይ መሆኑን አምባሳደር ታዬ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የውጭ ዲፕሎማሲ በአብሮነትና የጋራ ተጠቃሚነት ላይ ያተኮረ መሆኑን ጠቅሰው ከብሔራዊ ጥቅም ባሻገር የአፍሪካን ጥቅምና ፍላጎት ማስጠበቅን መሰረት ባደረገ መልኩ የዲፕሎማሲ ጥረቷን አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል።
ከብሔራዊ እና የአፍሪካን ጥቅም ከማስጠበቅ ባለፈ ችግሮችን በአፍሪካውያን አቅም የመፍታት መርህ እንዲተገበርም አበክራ ትሰራለች ነው ያሉት።
በቀጣይም የኢትዮጵያን ውስጣዊ አንድነትና ጥንካሬ በማጎልበት በዲፕሎማሲው መስክም አቀሟን ለማጉላት በጋራ መስራት አለብን ብለዋል።