ቀጥታ፡

መንግስት በገባው ቃል መሰረት አየር መንገዱ ወደ መቀሌ መደበኛ በረራ መጀመሩ ልዩ የደስታ ስሜት ፈጥሮልናል-- ኢዜአ በመቀሌ በመገኘት ያነጋገራቸው መንገደኞች

ታህሳስ 19/2015 መንግስት በገባው ቃል መሰረት አየር መንገዱ ወደ መቀሌ መደበኛ በረራ መጀመሩ ልዩ የደስታ ስሜት ፈጥሮልናል ሲሉ ኢዜአ በመቀሌ በመገኘት ያነጋገራቸው መንገደኞች ገለጹ።

የሠላም ሥምምነቱን ተከትሎ መንግሥት በገባው ቃል መሰረት የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዛሬው ዕለት ወደ መቀሌ መደበኛ በረራ ጀምሯል።

በዚህም የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ዛሬ ከቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ መንገደኛችን አሳፍሮ ወደ መቀሌ አምርቷል።

የሠላም ሥምምነቱን ተከትሎ አየር መንገዱ ወደ መቀሌ ዳግም በረራ መጀመሩ መንግሥት ለሠላም ሥምምነቱ ተግባራዊነት ያለውን ቁርጠኝነት ያረጋገጠ መሆኑ ተገልጿል።  

ኢዜአ ያነጋገራቸው መንገደኞች "አየር መንገዱ ወደ መቀሌ ዳግም በረራ በመጀመሩ "ቤተሰቦቻችንንና  ወዳጆቻችንን እንድናገኝ ስለረዳን ትልቅ ደስታ ፈጥሮልናል" ብለዋል።

መንግሥት ወደ መቀሌ ዛሬ የጀመረውን በረራን ጨምሮ በክልሉ ሌሎችም አገልግሎቶችን ዳግም ለማስጀመር እየሰራ ያለው ሥራ የሚበረታታ መሆኑንም ነው ያነሱት።     

በዛሬው ዕለት የተጀመረው ዳግም በረራ ለመላው ኢትዮጵያዊያን ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑን ገልጸው በተመሳሳይ ሌሎችም አገልግሎቶች ሙሉ በሙሉ እንዲጀመሩ አሁንም መንግሥት የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ነው የተናገሩት።  

ከቀናት በፊት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ የተመራ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ልዑክ ወደ መቀሌ በማቅናት እነዚህና መሰል አገልግሎቶችን ማሳለጥ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከሕወሃት አመራሮችና ከመቀሌ ነዋሪዎች ጋር ውይይት ማድረጋቸው ይታወሳል።

በውይይቱ ወቅትም ነዋሪዎቹ ተቋርጦ የነበረው መደበኛ የአውሮፕላን በረራ ዳግም እንዲጀመር መጠየቃቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም