ቀጥታ፡

በተለዋዋጩ ዓለም አቀፋዊና ቀጣናዊ ፈተናዎች ውስጥ የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስከበር በጋራ መቆም አለብን

አዲስ አበባ /ኢዜአ/ ታህሳስ 19/2015 በተለዋዋጩ ዓለም አቀፋዊና ቀጣናዊ ፈተናዎች ውስጥ የኢትዮጵያን አንድነትና ጥቅም ለማስከበር በጋራ መቆም አለብን ሲሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ሚኒስትር አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ገለጹ።

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባላት ተሳታፊ ፖለቲከኞችም የተደረሰው የሰላም ስምምነት ለአገር ትልቅ ተስፋ ፈጥሯል ብለዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች በሰሜን ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የተደረሰውን የሰላም ስምምነት በተመለከተ ውይይት አካሂደዋል

ከዚህ ቀደም "የአገረ-መንግሥት ግንባታና የምሁራን ሚና" በሚል መሪ ሃሳብ  የዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንቶች፣ የምርምር ተቋማት ኃላፊዎችና ሌሎችንም ያካተተ ሀገራዊ የምሁራን የምክክር መድረክ ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር መካሄዱ ይታወሳል፡፡

የዚህ መርሀ ግብር አካል የሆኑ የውይይት መድረኮች ዛሬም የተካሄዱ ሲሆን የፖለቲካ ፓርቲዎች በሰሜን ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የተደረሰውን የሰላም ስምምነት በተመለከተ ውይይት አድርገዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ሚኒስትር እና የሰላም ስምምነቱ የመንግስት ተደራዳሪ ቡድን አባል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፤ በቅድመ ጦርነት የነበሩ አገራዊ ፈተናዎች፣ የሪፎርም እርምጃዎች እንዲሁም ስለ ሰላም ስምምነቱ ይዘትና የትግበራ ሂደት ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ተለዋዋጭ በሆነው ዓለም አቀፋዊና ቀጣናዊ ፈተናዎች ውስጥ የኢትዮጵያን አንድነትና ጥቅም ለማስከበር በጋራ መቆም አለብን ሲሉ ተናግረዋል።

ፖለቲካ በሀሳብ ግብይት ሳይሆን በቲፎዞ አካሄድ ለአሁናዊ አገራዊ ጉዞ አደጋ በመሆኑ ችግሩን ለመቅረፍና አገርን ወደ ፊት ለማራመድ የጋራ ጥረትን ይጠይቃል ብለዋል።

የሰላም ስምምነቱ በብዙ ችግር ውስጥ ለቆየው ህዝብ ትልቅ ዕፎይታ እና ተስፋ የሰጠ ነው ያሉት አንባሳደር ሬድዋን፤ የስምምነቱ ትግበራ በተጀመረው አግባብ በጥንቃቄ ይከወናል ብለዋል።

በዚህ የመንግስት ጥረት የኢትዮጵያ ሰላም እንዲደናቀፍ የሚሰሩ ሃይሎችን መታገል የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሚና ሊሆን ይገባል ነው ያሉት።

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ዶክተር መብራቱ ዓለሙ፤ በደቡብ አፍሪካ የተደረሰው የሰላም ስምምነትና የእስካሁኑን ትግበራ የጋራ ምክር ቤቱ በአድናቆት የተመለከተው መሆኑን ገልጸዋል።

ሰላም አማራጭ የሌላው ጉዳይ በመሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሰላም እና ለሀገረ መንግስት ግንባታ ትልቅ ሚና እንዳላቸው ገልፀው የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሰላም ስምምነቱ ተግባራዊነት ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የውይይቱ ተሳታፊ ፖለቲከኞችም የተደረሰው የሰላም ስምምነት ለአገር ትልቅ ተስፋ መሆኑን ከትግበራው ጋር የተያያዙ ሃሳቦችን አንስተው ተወያይተዋል።

በሌሎች አካባቢዎችም ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ተመሳሳይ ፖለቲካዊ መፍትሄዎች ያስፈልጋሉ ብለዋል።

በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ዶክተር ዓለሙ ስሜ፤ ኢትዮጵያን የገጠሟትን ፈተናዎች የፖለቲካ ልሂቃን በጋራ መመከት አለባቸው ብለዋል።

የሰሜኑን ግጭት ለመፍታት እንደተደረሰው የሰላም ስምምነት ሁሉ ሌሎች ችግሮችም በሰማዊ መንገድ ለመፍታት የመንግስት ቁርጠኝነት መኖሩን አረጋግጠዋል።

የፕሪቶሪያውን የሠላም ስምምነት ተከትሎ መንግስት የቴሌኮም፣ መብራት፣ ባንክ፣ የአየር ትራንስፖርትና ሌሎችም አገልግሎቶችን በማስጀመር የተጠናከረ የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት ተደራሽ እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም