በኢትዮጵያ በስደት ላይ ለሚገኙ 150 ኤርትራውያን የከፍተኛ ትምህርት እድል ሊሰጥ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ በስደት ላይ ለሚገኙ 150 ኤርትራውያን የከፍተኛ ትምህርት እድል ሊሰጥ ነው
ሽሬ እንዳስላሴ መስከረም 21/2011 በኢትዮጵያ በስደት ላይ ከሚኖሩ ኤርትራውያን መካከል 150 ተማሪዎች በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ገብተው የመማር ዕድል እንደሚያገኙ በኢትዮጵያ የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ አስተዳደር አስታወቀ። በተያዘው ዓመት ሌሎች ቁጥራቸው ከ11ሺህ በላይ የሆኑ ህጻናት የቅድመ መደበኛ ትምህርት ዕድል ማግኘታቸውም ተመልክቷል። በኢትዮጵያ የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ አስተዳደር የሰሜን ጽህፈት ቤት የትምህርት ኦፊሰር አቶ ኤፍሬም ሀጎስ ለኢዜአ እንደገለጹት ከ180 ሺህ የሚበልጡ ኤርትራውያን ስደተኞች በተለያዩ መጠለያ ጣቢያዎች ይገኛሉ፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ ኤርትራውያን ስደተኞች መካከል 150 ተማሪዎች ዘንድሮ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በነጻ ለመማር እድል እንደሚሰጣቸውም ተናግረዋል፡፡ ወደ ከፍትኛ ትምህርት ተቋማት የሚገቡ 280 ስደተኞች የመግቢያ ፈተና እንዲወስዱ መደረጉንና በአሁኑ ወቅት ፈተናውን ያለፉ 150 ተማሪዎች መለየታቸውን አስረድተዋል፡፡ ፈተናውን ያለፉ 150 ስደተኞችም በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርታቸውን እንደሚከታተሉም ነው አቶ ኤፍሬም የገለጹት። ኤርትራውያን ስደተኛ ተማሪዎች በኢትዮጵያ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ መደረጉ በሁለቱ አገራት መካከል አሁን የተጀመረውን ሰላማዊ ግንኙነት ይበልጥ እንደሚያጠናክረውም ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ለኤርትራውያን ስደተኞች የትምህርት ዕድል ሲሰጥ የአሁኑ ለሰባተኛ ጊዜ ሲሆን በየዓመቱ ከ100 ያላነሱ ተማሪዎችም የዕድሉ ተጠቃሚ ሆነዋል። በተመሳሳይ በትግራይ ክልል በሚገኙ አራት የኤርትራውያን ስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ 11ሺህ 87 ኤርትራውያን በቅድመና በመደባኛ ትምህርት እንዲሁም በሙያ ክህሎት ማበልጸጊያ እንዲማሩ መደረጉን አቶ ኤፍሬም አክለው ተናግረዋል፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ከአገራቸው ተሰደው ወደኢትዮጵያ ቢመጡም ልጆቻው እዚህ የትምህርት ዕድል በማግኘታቸው መደበኛ ትምህርታቸውን መቀጠላቸውን የተናገሩት ደግሞ በማይዓይኒ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ የሚገኙት አቶ ተስፋልደት ይህደጎ የተባሉ ስደተኛ ናቸው፡፡ በአዲ ሓሩሽ መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ሌላው ስደተኛዋ ወይዘሮ ለምለም ዘካሪያስ እንደተናገሩት በአካባቢያችን የሚገኙ ትምህርትቤቶች ለኤርትራውያን ተማሪዎች በራቸው ክፍት መሆኑ ትልቅ እድል መሆኑን ገልጸዋል፡፡ "ልጆቻቸው ከኢትዮጵያውያን ወንደሞቻቸው ጋር በአንድ ክፍል ውስጥ እንዲማሩ መደረጉ በሁለቱ አገራት ህዝቦች መካከል ጠንካራ ግንኙነት ለመፍጠር ለሚደረገው ጥረት የላቀ አስተዋፅኦ አለው" ብለዋል። የኢትዮጵያ መንግስት ለኤርትራውያን ስደተኞች እየሰጠ ያለው የከፍተኛ የትምህርት እድል ለሌሎች አገራት በመልካም አርአያነት የሚጠቀስ መሆኑን የገለጸው ደግሞ ወደ ዩኒቨርሲቲ ለማግባት የመግቢያ ፈተና የወሰደው ተማሪ ዓንዶም ፍሳሃየ ነው።