ቀጥታ፡

የፌደራል መንግስት ልዑካን የመቀሌ ጉብኝት መንግስት የተጓዘበት መንገድ ውጤት እያመጣ መሆኑን ያሳየ ነው - የአገር ሽማግሌዎች

አዳማ (ኢዜአ) ታህሳስ 19/2015 በመቀሌ የተደረገው የፌዴራል መንግስት ልዑካን ጉብኝት መንግስት የተጓዘበት መንገድ ውጤት እያመጣ መሆኑን ያሳየ ነው ሲሉ የአገር ሽማግሌዎች ተናገሩ

በመቀሌ የተደረገው የፌዴራል መንግሰት ልዑካን ጉብኝት ተነፋፍቀው የቆዩ የቤተሰብ አባላትን ከማገናኘቱ ባለፈ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን የሚያጠናክር አዲስ ምዕራፍ የከፈተ መሆኑን የአዳማ ከተማ የሀገር ሽማግሌዎች ገለጸዋል።

የፌዴራል መንግስት ልኡካን ጉብኝትና ፍሬያማ ውይይት ተከትሎ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በመቀሌ መደበኛ በረራውን ጀምሯል፤ በዚህም ተለያይተው የቆዩ ቤተሰቦች እንዲገናኙ መልካም አጋጣሚ ፈጥሯል ብለዋል አስተያየት ለኢዜአ የሰጡ የአገር ሽማግሌዎች።

ከአዳማ ከተማ የሀገር ሽማግሌ መካከል አቶ ፈይሳ መገርሳ እንደገለፁት ወልዶ ማሳደግ፣ ሰርቶ ማግኘት፣ ወጥቶ መግባት፣ መልማትና ማደግ የሚቻለው ሰላም ሲኖር ነው ብሎ መንግስት የተጓዘበት መንገድ ውጤት እያመጣ ነው ብለዋል።

ጉብኝቱ በጦርነቱ ምክንያት ሳይገናኙ የቆዩ የቤተሰብ አባላትን የሚያገናኝ ከመሆኑም ባለፈ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትና ትስስሩን የሚያጠናክር አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ነው ብለዋል።

"ሰላም የአንድ ወገን ብቻ ተደርጎ መወሰድ የለበትም" ያሉት አቶ ፈይሳ፤ የበለጠ ፍሬውን ለማጣጣም ሁሉም ወገኖች አንድ አይነት እርምጃ ልኖራቸው ይገባል ብለዋል።

ይህን ተከትሎ ባንክ እንዲከፈት፣ትምህርት ቤቶች ማስተማር እንዲጀምሩ፣ ማህበረሰቡ እንዲገናኝ ከማድረግ አኳያ የጉብኝቱ ሚና የጎላ ነው ብለዋል።

ሰላምን የሚያፀናው መንግሰት ብቻ አይደለም ያሉት አቶ ፈይሳ፤ ማንኛውም ሰላም ፈላጊ ህዝብ አሁንም ለውጤታማነቱ ከመንግስት ጎን በመሆን የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ጥቃቅን ነገሮችን እንደ ቅሬታና ጉድለት ማንሳት የለብንም ተቀራርበን ተግባብተን የህዝባችንን ሰላምና ተጠቃሚነት ወደ መሬት ማውረድ አለብን ነው ያሉት።

"እኛ አንድ ህዝብ ነን፣ ተጋብተናል፣ ተዋልደናል መለያየት የለብንም ያሉት የአገር ሽማግሌው፤ መንግስት ከፍተኛ የልዑካን ቡድኑን ትግራይ ድረስ በመላክ ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት የገለፀበትን ሂደት ሁላችንም ከመንግስታችን ስንጠብቀው የነበረና የሚደገፍ ቀዳሚ ተግባር ነው ብለዋል።

የአዳማ ከተማ የሀገር ሽማግሌዎች ጉባዔ ሰብሳቢ ሃጂ ሁሴን ሃሞ በበኩላቸው የሰላም ስምምነቱ ከብዙ ውጣ ውረደ በኋላ የመጣው ውጤት በመሆኑ ደስተኞች ነን ብለዋል።

በመቀሌ የነበረው ጉብኝትና ፍሬያማ ውይይት ለሰላም የነበረንን ናፍቆት እውን ያደረገ ነው ያሉት ሃጂ ሁሴን፤ በዚህም ህዝቡ ተደስቷል የተነፋፈቀው ተገናኝቷልና ይህ የሚደገፍ ሀሳብ ነው ብለዋል።

አሁን የተደረሰው የሰላም ስምምነትና እያየን ያለነው ውጤት ለኢትዮጵያ ብቻም ሳይሆን ለሌሎችም ምሳሌ የሚሆን ነው ያሉት ሃጂ ሁሴን፤ መገፋፋት፣ መለያየት፣መናናቅና ጥላቻን ለማስወገድ አዲስ በር የከፈተ ጉብኝት መሆኑንም ገልጸዋል።

በዚህም በህዝቦች መካከል በፊት የነበረውን ፍቅርና አንድነት ዳግም እውን ለማድረግ ቁልፍ አጋዥ መሆኑን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም