የታክስ አሰባሰብ ሥርዓቱን በማዘመን የተለያዩ ወጪዎችን ከሚመነጨው ገቢ ግብር ለመሸፈን እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የታክስ አሰባሰብ ሥርዓቱን በማዘመን የተለያዩ ወጪዎችን ከሚመነጨው ገቢ ግብር ለመሸፈን እየተሰራ ነው
ታኅሳስ 19/2015(ኢዜአ) የታክስ አሰባሰብ ሥርዓቱን በማዘመንና በቴክኖሎጂ በማገዝ የወጪ ፍላጎታቸውን ከሚያመነጩት ገቢ ግብር ለመሸፈን እየሰሩ መሆኑን የክልሎች ገቢ ቢሮ ኃላፊዎች ገለጹ፡፡
የሐረሪ፣ የአፋር እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ የገቢዎች ቢሮ ኃላፊዎች ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ በክልሎቻቸው ውስጥ የሚገኙ የገቢ አማራጮችን ለማስፋትና አሟጦ ለመሰብሰብ እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የሐረሪ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ አቶ በቀለ ተመስገን ባለፉት አምስት ወራት በክልሉ ከዕቅድ በላይ ገቢ መሰብሰቡን ገልጸዋል፡፡
ለወደፊትም በክልሉ የውስጥ አቅምን በማጠናከር ለልማት የሚውሉ ወጪዎችን በገቢ ለመሸፈን ዕቅድ ተይዞ ወደ ተግባር መገባቱን ገልጸው፤ አሁን ላይ የክልሉን 40 በመቶ ወጪ በገቢ መሸፈን መቻሉንም ተናግረዋል፡፡
በቀጣይ የታክስ አሰባሰብ ሥርዓቱን በማዘመንና በቴክኖሎጂ የታገዘ በማድረግ ለዕቅዱ ተግባራዊነት የሚረባረቡ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የአፋር ክልል ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ አቶ መሐመድ ሐሰን በበኩላቸው፤ በክልሉ የሚሰበሰበውን ገቢ ለማሳደግ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር የሚመራ ግብረ-ኃይል ተደራጅቶ ወደ ትግበራ ተገብቷል፡፡
በዚህም ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ ከመሰብሰብ አንጻር እና ተጨማሪ የገቢ አማራጮችን በማስፋት ረገድ ሰፊ ሥራ መሰራቱንም ገልጸዋል፡፡
በተያዘው በጀት ዓመት 3 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ ዕቅድ መያዙን አመልክተው የአምስት ወራት አፈጻጸም የዕቅዱን ስኬት ያመላከተ ነው ብለዋል፡፡
የክልሉን የወጪ ፍላጎትም በውስጥ ገቢ ለመሸፈን አቋም ተይዞ ወደ ትግበራ መገባቱን ጠቁመዋል፡፡
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ገቢዎች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር መለስ ኪዊ፤ በክልሉ ከዓመት ዓመት የሚሰበሰበው ገቢ ከፍ እያለ መጥቷል፡፡
ሆኖም አሁን የተሻለ ገቢ ለመሰብሰብ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡