ቀጥታ፡

የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ከመመሪያ ውጭ የሚፈጸሙ ግዥዎች ላይ ማስተካከያ ሊያደርግ ይገባል- ምክር ቤቱ

ታህሳስ 19/2015(ኢዜአ) የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት፣ የኬሚካልና የኮንስትራክሽን ግብዓቶች ኢንዱስትሪ ምርምርና ልማት ማዕከል ከመመሪያ ውጭ የሚፈጸሙ ግዥዎች ላይ ማስተካከያ ሊያደርግ እንደሚገባ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።

የምክር ቤቱ የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የተቋሙን የ2013 በጀት ዓመት ሂሳብ ኦዲት ሪፖርት ላይ የተወያየ ሲሆን የምክር ቤቱ አባላት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ተቋሙ የዕቃ፣ የግንባታ እና አገልግሎት ግዥዎችን ሲፈጽም መመሪያው በሚያዘው መሰረት በግልጽ ጨረታ የግዥ ዘዴ ተወዳዳሪዎችን አጫርቶ ከአሸናፊ ድርጅቶች ጋር ውል በመግባት ግዥውን መፈጸም አለመቻሉ በቀረበው ኦዲት ግኝት ተጠቅሷል።    

በዚህም ከመመሪያ ውጭ 1 ሚሊየን 226 ሺህ በውስን የጨረታ ግዥ ተፈጽሞ በኦዲት ግኝቱ መታየቱም ተነስቷል።

የገንዘብ ሚኒስቴር ታህሳስ 12 ቀን 2008 ዓ.ም የፌደራል መንግሥት ግዥ አፈጻጸም መመሪያ እንደገና ለማሻሻል ባወጣው መመሪያ መሰረት ግዥ መከናወኑ ሲጣራ 88 ሺህ 847 ብር የዕቃና አገልግሎት ግዥው በዋጋ ማወዳደሪያ መከናወን ሲገባው በቀጥታ ግዥ ተፈጽሞ በኦዲት ግኝቱ መታየቱም ተገልጿል።

ከዚህ ባለፈም የፌደራል መንግሥት የገንዘብ ክፍያ መመሪያ የዕቃው ወይም የአገልግሎቱ ተፈላጊ ባህሪያት ዝርዝር ወይም ስፔሲፊኬሽን መሰረት መቅረቡን ወይም አገልግሎት መሰጠቱን መረጋገጥ እንዳለበት ቢያዝም በተፈላጊ ባህሪያት ዝርዝር መሰረት መቅረቡ ሳይረጋገጥ ለተፈጸመ ግዥ በድምሩ 1 ሚሊየን 14 ሺህ ተከፍሎ መገኘቱም መመሪያን የተከተለ አለመሆኑንም ተጠቁሟል።  

ተቋሙ ከንብረት አያያዝ ጋር በተያያዘ የነዳጅ ኩፖን አጠቃቀምና መገልገያ ቁሳቁሶች አያያዝ ላይ ክፍተቶች መኖራቸውም ተመላክቷል።  

የምክር ቤቱ አባላት በሰጡት አስተያየት ተቋሙ መመሪያን የተከተሉ የግዥ ሥርዓት ሊከተል እንደሚገባ አንስተው በግዥ የሚያስገባቸው ቁሳቁሶች ጥቅም ላይ መዋላቸውን ማረጋገጥ እንደሚገባውና የሚከተለው አሰራር ለሙስና የተጋለጠ እንዳይሆን መጠንቀቅ እንደሚገባ አሳስበዋል።  

ከአበል ክፍያ ጋር በተያያዘ ሕግን ያልተከተሉ ክፍያዎች መኖሩም ሊስተካከል የሚገባው ሌላው የኦዲት ግኝት መሆኑም በውይይቱ ላይ ተነስቷል።   

የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ወይዘሮ አሬሬ ሞሲሳ እንደተናገሩት፤ ተቋሙ በኦዲት ግኝቱ የቀረቡ ምክረ-ሃሳቦችን ለማስተካከል በትኩረት መሥራት አለበት።

ግዥዎች ከመፈጸማቸው በፊት በአግባቡ መታቀድ እንዲሁም ሕግና ሥርዓትን የተከተለ አሰራር መዘርጋት እንደሚገባ ጠቁመው "የኦዲት ግኝቱን መሰረት በማድረግ ተጠያቂ መሆን የሚገባቸው አካላት መጠየቅ መቻል አለባቸው" ሲሉም ነው አጽንኦት የሰጡት። 

ተመላሽ መሆን ያለበት የመንግሥትና የሕዝብ ኃብትም ሕጉ በሚያዘው መሰረት ተመላሽ መሆን እንዳለባቸውም አሳስበዋል።   

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል በሰጡት ምላሽ፤ በፌደራል ዋና ኦዲተር የቀረቡ የኦዲት ግኝቶች በቀጣይ ለሚወሰዱ ማስተካከያ እርምጃዎች ግብዓት የሚሆኑ ናቸው ብለዋል።  

አላስፈላጊ ወጪዎች መቀነስ ይገባል ያሉት ሚኒስትሩ በዚህ ላይ የተፈጠሩ ችግሮችን ለማስተካከል አስፈላጊው እርምጃ እንደሚወሰድ አረጋግጠዋል።   

"ለውሎ አበል ክፍያ በሚል 2 ሚሊየን 960 ሺህ ብር የተፈጸመው ክፍያ የሥነ-ምግባር ክትትል የሚያስፈልገው ነው፤ በቀጣይ የሚጣራ ይሆናል" ብለዋል።

የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ክርስቲያን ታደለ በሰጡት ማጠቃለያ፤ ተቋሙ የኦዲት ማሻሻያ መርሃ-ግብር እስከ ታህሳስ 30 ቀን 2015 ዓ.ም እንዲያቀርብ አሳስበው የኦዲት ግኝት ማሻሻያ ሪፖርትም በየሩብ ዓመቱ መላክ እንዳለበትም ነው ያስገነዘቡት።  

ሕግና መመሪያዎች በጣሱ አመራሮችና ባለሙያዎች ላይ የገንዘብ ሚኒስቴር እስከ ጥር 8 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ አስተዳደራዊ እርምጃዎች ወስዶ ለቋሚ ኮሚቴው እንዲያሳውቅ አቅጣጫ ሰጥተዋል።    

"የፍትሕ ሚኒስቴር የኦዲት ግኝቱን መነሻ በማድረግ በፍትሐብሔርና በወንጀል የሚያስጠይቁ ጉዳዮች ካሉ በቂ ምርመራ በማድረግ በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ እንዲያሳውቀን እንፈልጋለን" ሲሉ ሰብሳቢው አቅጣጫ ሰጥተዋል።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም