አየር መንገዱ ወደ መቀሌ መደበኛ በረራ መጀመሩ የሰላም ሂደቱን ወደ ተሻለ ምዕራፍ ያሸጋገረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
አየር መንገዱ ወደ መቀሌ መደበኛ በረራ መጀመሩ የሰላም ሂደቱን ወደ ተሻለ ምዕራፍ ያሸጋገረ ነው
ታኅሳስ 19/2015(ኢዜአ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ መቀሌ በረራ መጀመሩ የሰላም ሂደቱን ወደ ተሻለ ምዕራፍ ያሸጋገረ መሆኑን ዛሬ በተጀመረው መደበኛ በረራ ወደ መቀሌ ያቀኑ መንገደኞች ገለጹ፡፡
የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ መንግስት በገባው ቃል መሰረት የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዛሬው እለት ወደ መቀሌ መደበኛ በረራ ጀምሯል።
በዚህም የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ዛሬ ከቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ መንገደኞችን አሳፍሮ ወደ መቀሌ አምርቷል።
የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ አየር መንገዱ ወደ መቀሌ ዳግም በረራ መጀመሩ መንግስት ለሰላም ስምምነቱ ተግባራዊነት ያለውን ቁርጠኝነት ያረጋገጠ መሆኑም ነው የተገለጸው፡፡
ኢዜአ ያነጋገራቸው መንገደኞች አየር መንገዱ ወደ መቀሌ ዳግም በረራ በመጀመሩ መደሰታቸውን ጠቅሰው፤ ይህም የሰላም ሂደቱን ወደ ተሻለ ምዕራፍ ያሸጋገረ ስለመሆኑ ተናግረዋል።
መንግስት ለሰላም ስምምነቱ ተግባራዊነት እያከናወነ ያለውን ስራ አድንቀው፤ በቀጣይ ስምምነቱን ተግባራዊ በማድረግ ረገድ የተጀመሩ ስራዎች ይበልጥ ተጠናክረው እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡
በቅርቡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ ታገሰ ጫፎ የተመራ የፌደራል መንግስት ከፍተኛ አመራሮች ልዑክ ወደ መቀሌ ማቅናቱን ተከትሎ ሁኔታዎች በፍጥነት እየተሻሻሉ መሆኑንም በማውሳት በቀጣይም ለሰላም ስምምነቱ ተግባራዊነት በሚደረጉ ተግባራት ላይ ሁሉም የሚጠበቅበትን ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባ ነው የተናገሩት፡፡
ከቀናት በፊት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የተመራ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ልኡክ ወደ መቀሌ በማቅናት እነዚህና መሰል አገልግሎቶችን ማሳለጥ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከህወሃት አመራሮችና ከመቀሌ ነዋሪዎች ጋር ውይይት ማድረጋቸው ይታወሳል።
በውይይቱ ተቋርጦ የነበረው መደበኛ የአውሮፕላን በረራ ዳግም እንዲጀመር ነዋሪዎቹ መጠየቃቸው ይታወቃል፡፡