ህገወጥ የሰዎች ዝውውር አምራች ትውልድ ያሳጣል፣ የአገር ገጽታን ያበላሻል - ኢዜአ አማርኛ
ህገወጥ የሰዎች ዝውውር አምራች ትውልድ ያሳጣል፣ የአገር ገጽታን ያበላሻል
ወልዲያ መስከረም 21/2011 ህገወጥ የሰዎች ዝውውር አምራቹን ትውልድ የሚያሳጣና የአገር ገጽታን የሚያበላሽ ነው ሲል የአማራ ክልል ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ገለጸ። በአገር አቀፍ ከሚስተዋለው ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር የአማራ ክልል ከግማሽ በላይ እንደሚሸፍን በወልድያ ከተማ በተካሄደ የውይይት መድረክ ላይ ተገልጿል። የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ጥላሁን መኳንንት በመድረኩ ላይ እንደተናገሩት ህገ ወጥ ስደት ዓለም አቀፍ ወንጀል በመሆኑ የመከላከል ተግባሩ ለመንግሥት ብቻ የሚተው አይደለም። በኢትዮጵያ በየዓመቱ 130ሺህ ህገ ወጥ ስደተኞች ከአገር እንደሚወጡ ችግሩን አሳሳቢ እንደሚያደርጉት ገልጸዋል። ከዚህ ውስጥም 72ሺህ ለሚሆኑት ስደተኞች መነሻቸው ከአማራ ክልል ሲሆን፣ ዋና መተላለፊያዎቹም ባቲና መተማ ናቸው፡፡ ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል ከክልል እስከ ቀበሌ ምክር ቤት ተቋቁሞ ግንዛቤ በመፍጠር ላይ እንደሚገኝ አቶ ጥላሁን ተናግረዋል። ይሁን እንጂ ኅብረተሰቡ በደላሎች የሚከናወኑ ተግባራትን ለሚመለከታቸው አካላት በመጠቆም ትብብር ስለማያደርግ ውጤት ማምጣት አልተቻለም ብለዋል። በዚህ ዓመት ድርጊቱን በመከላከል ሥራው ለውጥ ለማምጣት ኅብረተሰቡን፣ የመንግስት አካላትን፣ ዕድሮችን፣ የፍትህ አካላትንና የሃይማኖት መሪዎችን ያሳትፋል። በቅርቡ በህጋዊ መንገድ ሰራተኞችን ወደ ውጭ መላክ ለመጀመር ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይና የስምንተኛ ክፍል ትምህርትን ያጠናቀቁት ሥልጠና ያገኛሉ። ከአማራ ክልል በህገ ወጥ ስደት በይበልጥ የተጠቃው የምስራቅ አማራ በመሆኑ ችግሩን ለመፍታት ከአውሮፓ ኅብረት ጋር ተባብሮ መስራት መጀመሩን ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡ የሰሜን ወሎ ዞን የፍትህ መምሪያ ኃላፊና የህገ ወጥ ስደት ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ አምባው መልኬ እንዳሉት የህገ ወጥ ስደት በርካታ ገፊና ሳቢ ምክንያቶች አሉት። የኅብረተሰቡ የአመለካከትና አስተሳብ ችግሮች፣ ድህነት፣ የደላሎች ባልተጨበጠ ተስፋ ማታለል፣ የአቻ ለአቻና የቤተሰብ ግፊት፣ የፖለቲካ አለመረጋጋት ዋነኞቹ ምክንያቶች መሆናቸውን ገልጸዋል። ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር በዜጎች ህይወትና አካልና ንብረት እያደረሰ ያለው ጉዳት የጋራ እንደሆነ ሁሉ፤ የመከላከል ሥራውም የጋራ መሆን ይገባዋል ብለዋል። ለዚህም የመንግሥት አካላት አሰራራቸውን በማጥበቅ በህገ ወጥ ደላሎችና ተባባሪዎቻቸው ላይ አስተማሪ እርምጃ መውሰድ አለባቸው። የወልድያ ከተማ ነዋሪው ሃጂ አብደላ ያሲን በሰጡት አስተያየት በመድረኩ ህገ ወጥ ስደት የሚያስከትለውን ችግር ለማስገንዘብ በፊልምና በፎቶ ታግዞ የተካሄደው የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ የሚያመሰግን ነው። ህዝቡ ደላሎችን የሚፈራቸው ከመንግሥት አካላት ግንኙነት ስላላቸው ነው ያሉት ሃጂ አብደላ፤ ፍርድ ቤት የሚቀርቡም ሆነ በኬላ የሚያስተላልፉ ደላሎችን በድርድር መልቀቅ መቆም ይገባዋል ይላሉ። ''እኔም እንደ ሃይማኖት መሪነቴ የህገ ወጥ ስደት እያስከተለ ያለውን ጉዳት ለወጣቱና ለሌላውኅብረተሰብ አስተምራለሁ''ሲሉም ቃል ገብተዋል። በመድረኩ የወጣቶችና የሴቶች ማህበራት፣ የዞንና የከተማው አመራሮች፣ የሃይማኖትና የዕድር መሪዎች፣ የአገር ሽማግሌዎችና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።