የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለአፍሪካ እግር ኳስ ሻምፒዮና የሚያደርገውን ዝግጅት ዛሬ ጀምሯል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለአፍሪካ እግር ኳስ ሻምፒዮና የሚያደርገውን ዝግጅት ዛሬ ጀምሯል
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 19/2015 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአልጄሪያ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው ሰባተኛ የአፍሪካ እግር ኳስ ሻምፒዮና(ቻን) የሚያደርገውን ዝግጅት ዛሬ ጀምሯል።
በአገር ውስጥ ሊግ የሚሳተፉ ተጫዋቾች ብቻ የሚሳተፉበት ውድድር ከጥር 5 እስከ 27 ቀን 2015 ዓ.ም የሚካሄድ ሲሆን ኢትዮጵያን ጨምሮ 18 አገራት ይካፈላሉ።
ዋልያዎቹ በምድብ አንድ ከአስተናጋጇ አልጄርያ፣ሞዛምቢክ እና ሊቢያ ጋር ተደልድለዋል።
የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ለቻን ውድድር ቅድመ ዝግጅት ጥሪ ካደረጉላቸው 42 ጊዜያዊ ተጫዋቾች መካከል 14 ቀንሰው ለ28 ተጫዋቾች በድጋሚ ጥሪ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው።
ጥሪ የተደረገላቸው 28 ተጫዋቾች ትናንት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ተገኝተው ሪፖርት ያደረጉ ሲሆን የአካል ብቃት እና የጤና ምርምራ ተደርጎላቸዋል።
ብሔራዊ ቡድኑ ተጫዋቾች ዛሬ ሲኤምሲ በሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ስፖርት ሜዳ ልምምድ ማድረግ ጀምረዋል።
በዛሬው ልምምድ ላይ የወልቂጤ ከተማው ጌታነህ ከበደ እና የፋሲል ከነመው ታፈሰ ሰለሞን አለመገኘታቸውን አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ገልጿል።
የመጀመሪያ ቀን ልምምዱ የተጫዋቾችን ወቅታዊ ብቃት መገምገም ላይ ያተኮረ ነበር ብሏል።
ብሔራዊ ቡድኑ እስከ ታህሳስ 26 ቀን 2015 ዓ.ም ልምምድ ካደረገ በኋላ በሞሮኮ ለአንድ ሳምንት ያህል ዝግጅቱን በማከናወን ወደ አልጄሪያ እንደሚያቀኑ ነው አሰልጣኝ ውበቱ የገለጸው።