ቀጥታ፡

ባለፉት 3 ዓመታት ከአንድ ሺህ በላይ አርሶ አደሮች የቡና ላኪነት ፈቃድ ተሰጥቷቸዋል-የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን

ታኅሳስ 19/2015(ኢዜአ) ባለፉት ሶስት ዓመታት ከአንድ ሺህ በላይ አርሶ አደሮች የቡና ላኪነት ፈቃድ ማግኘታቸውን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተር አቶ ሻፊ ኡመር ለኢዜአ እንዳሉት፤ ባለስልጣኑ ባለፉት አራት ዓመታት የሪፎርም ስራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡

የቡና ምርት ጥራትን ማስጠበቅ፡ የግብይት ስርዓቱን ማዘመንና በምርቱ ላይ እሴት መጨመር ምርታማነቱን ማሳደግ መቻላቸውን ገልጸዋል፡፡

በሪፎርሙ በቡና ግብይት ላይ ከፍተኛ እድገት በማምጣት የውጭ ምንዛሬ እንዲጨምር ተደርጓል ያሉት ኃላፊው ለአብነትም ባለፈው በጀት ዓመት 302 ሺህ ቶን ቡና ለውጭ ገበያ በመላክ 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር መገኘቱን አስታውሰዋል፡፡

የሪፎርም ስራዎች መተግበር ከጀመሩ ወዲህ ባሉ  አራት ዓመታት  ወደ ውጭ የተላከ የቡና ምርት በ104 ሺህ ቶን እድገት ማስመዝገቡንም ነው የገለጹት፡፡

ባለስልጣኑ የዓለም የቡና ገበያ ተለዋዋጭነትን መሰረት በማድረግ ተጨማሪ የገበያ መዳረሻዎችን የማፈላለጉን ስራ በትኩረት እያከናወነ መሆኑን እንደ ኤዥያ ባሉ አካባቢዎች አዳዲስ የገበያ መዳረሻዎችን ለማስፋት እንቅስቃሴ መጀመሩን ጠቁመዋል፡፡

በኢትዮጵያ ለውጭ ገበያ የምታቀርበው የቡና ምርት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን የገለጹት ምክትል ዳይሬክተሩ፤ ባለፉት ሶስት ዓመታትም ከአንድ ሺህ በላይ አርሶ አደሮች የቡና ላኪነት ፈቃድ አግኝተዋል ብለዋል፡፡

የቡና ላኪነት ፈቃድ ከወሰዱት አርሶ አደሮች መካከል ከ100 በላይ የሚሆኑ ቡናቸውን በቀጥታ ለውጭ ገበያ እንደሚያቀርቡም ገልጸዋል፡፡

በዘንድሮ በጀት ዓመት 360 ሺህ ቶን ቡና ወደ ውጭ በመላክ  2 ቢሊየን ዶላር ገቢ ለማግኘት ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም