መኖርያ አካባቢያቸውን ሁሉ በእጄ፤ ሁሉ በደጄ ያደረጉት ሚሊየነሯ አርሶ አደር

ታኅሳስ 19/2015(ኢዜአ) በሰሜን ሸዋ ዞን የሚኖሩት ሚሊየነሯ አርሶ አደር የመኖሪያ አካባቢያቸውን  ሁሉ በእጄ፤ ሁሉ በደጄ አድርገዋል።

ወይዘሮ አበራሽ ባሻህውረድ ይባላሉ በሰሜን ሸዋ ዞን ሞረትና ጅሩ ወረዳ የማንጉዶ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው።

በሚኖሩባት የገጠር ቀበሌ በሰብል ልማት፣ በአገልግሎት ዘርፉ፣ በቀላል ኢንዱስትሪውም ሁሉን በእጃቸው፤ ሁሉ በደጃቸው አድርገው ለአካባቢው ማኅበረሰብ የተሟላ አገልግሎት ይሰጣሉ።

የማንጉዶ ቀበሌ ነዋሪዎች በወይዘሮ አበራሽ በሻህውረድ ደጅ ጎራ ብለው የሚያጡት አገልግሎት የለም ቢባል ማጋነን አይሆንም፤ ወይዘሮ አበራሽ ሰብል በስፋት ያመርታሉ፤ እርሻቸውም በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ ነው።

ወፍጮ ተክለው ይፈጫሉ፤ ላሞችን አርብተው ወተት ያልባሉ፤ ንብ አንበው ማር ይቆርጣሉ፤ ሰንጋ አድልበው ለገበያ ያቀርባሉ፤ ዶሮ አርብተው እንቁላል ይሸጣሉ።

በአገልግሎት መስኩ ደግሞ ሱቅ ከፍተው ሸቀጣ ሸቀጥ ያቀርባሉ፤ ሬስቶራንት ከፍተው ምግብ እና መጠጥ ይሸጣሉ።

ወይዘሮ አበራሽ እስከ 12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን የተከታተሉ ሲሆን ሥራ ፈልጎ መቀጠር ሳይሹ፣ ከትንሽ ሱቅ ጀምረው፤ ግብርናቸውን አስፍተው፤ ዛሬ ከገጠር እስከ አዲስ አበባ የደረሰ በብዙ ሚሊየኖች የሚገመት ሀብት አካብተዋል።

በተሰማሩበት ሙያ ሁሉ ስኬታማ ነኝ የሚሉት ወይዘሮ አበራሽ ይህ ሁሉ ሲሆንም አንድም ጊዜ የብድር ዕዳ ገብተው እንደማያውቁና ሁሉንም ሥራ በራሳቸው ካፒታል እንደሚያንቀሳቅሱ ይናገራሉ።

ከዓመታት በፊት እርሻ ሲጀምሩ ከ50 ኩንታል የበለጠ አያመርቱም ነበር፤ ዘንድሮ ግን በስንዴ ልማት ብቻ ከ150 ኩንታል በላይ ምርት ይጠብቃሉ ብሎም ከአካባቢው አርሶ አደሮች እህል እየገዙ ይነግዳሉ።

ዘጠኝ ላሞችን ያልባሉ፤ እስከ 300 ሺህ ብር የገመቱትን ሰንጋ በሬ ጨምሮ እያደለቡ ሲሆን፤ የዶሮም ሆነ የንብ እርባታ ሥራቸውን እያሰፉ ነው።

በአንድ ወፍጮ ጀምረው ዛሬ አምስት የተለያዩ አገልግሎት የሚሰጡ ወፍጮዎችን በመትክል የአካባቢያቸው ነዋሪዎች ያለእንግልት በመንደራቸው አስፈጭተው እንዲመለሱ ትልቅ ዕድል ፈጥረዋል።

ለ24 ሰዓታት የሚሰሩ ሁለት የሰብል መውቂያ መኪናዎችን በመግዛት ከራሳቸው አልፈው በአካባቢው በብቸኝነት እያቀረቡ፤ ዘመናዊ ግብርና ዕውን እንዲሆን አድርገዋል።

"የማንሰራው ሥራ የለም፤ አቅማችን እስከፈቀደ ድረስ ሁሉንም እንሰራለን" የሚሉት አርሶ አደሯ፤ በአዲስ አበባ ከተማ በገዙት መሬት የወተት ላሞችን የማርባትና ሌሎች ኢንቨስትመንቶች ላይ የመሳተፍ ዕቅድ አላቸው።

ውሃ እጥረት ባይፈትናቸው በሰፈራቸው ሰፊ አትክልትና ፍራፍሬ በማልማትም ቀየውን የመመገብ ሃሳብ ይዘዋል።

ሌላው የአርሶ አደሯ መለያ የአካባቢውን ነዋሪ በሃሳብ በመደገፍ የሕብረተሰቡን አኗኗር በህብረት እንዲለውጡ እና ተደጋግፎ ማደግ ላይ ያላቸው ብርቱ መሻት ነው።

የማንጉዶ ቀበሌ የእንስሳት እርባታ ባለሙያው ወርቅነህ ጌታቸው፤ አበራሽ ባሻህውረድ በቀበሌው ሁሉንም አገልግሎት የሚያቀርቡ፤ ለወረዳው አርዓያ የሆኑ ሥራ ወዳድና ብርቱ ሴት እንደሆኑ ይገልጻሉ።

የአካባቢውን አርሶ አደሮች በማገዝ በጋራ እንዲለወጡ የሚተጉ እንደሆኑም ነው የመሰከሩት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም