''የኢትዮጵያን ዲፕሎማሲ ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ በተቋማት መካከል ያለው ቅንጅት መጠናከር አለበት''- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን - ኢዜአ አማርኛ
''የኢትዮጵያን ዲፕሎማሲ ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ በተቋማት መካከል ያለው ቅንጅት መጠናከር አለበት''- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን
ታኅሣሥ 18 /2015 የኢትዮጵያን ዲፕሎማሲ ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ በተቋማት መካከል ያለ ቅንጅት መጠናከር እንዳለበት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዋናው መስሪያ ቤት ፣ ተጠሪ ተቋማት እና ሚሲዮኖች የእቅድ አፈፃፀም ግምገማ ማጠቃለያ መርሃግብር ላይ ነው ።
በዚህ ጊዜም አገሪቱ ባለፉት ሁለት ዓመታት አበረታች ዲፕሎማሲያዊ ስኬቶችን በማስመዝገብ በሁለትዮሽ እና በባለብዙ ወገን መድረኮች ላይ ወሳኝ ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል።
አቶ ደመቀ ስለ ዲፕሎማሲ ስኬት ሲጠቅሱ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የተደረገውን ድርድር እንዲሁም የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነትን ያነሱ ሲሆን ኢትዮጵያ ጉዳዮችን ለመፍታት ባሳየችው ቁርጠኝነት "ለአፍሪካ ችግሮች የአፍሪካ መፍትሄዎች" በሚል መሪ ቃል የተሳካ ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል።
የዲፕሎማሲ ድል በጋራ እና በትብብር ስራ የሚመዘገብ መሆኑን ገልጸው የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ሌሎች የሀገሪቱ ሚኒስቴሮች እና በውጭ ሀገራት የሚገኙ የተለያዩ ሚሲዮኖች ቅንጅታዊ አሰራርና ትብብር በኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ላይ የጋራ የባለቤትነት ስሜትን ማጎልበት እና ቅንጅታዊ ስራዎችን ማጠንከር እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።
በሱሉልታ በቀጠለው የዛሬው መድረክ በትላንትናው ዕለት ቀርበው በነበሩ አመታዊው የእቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ላይ የተነሱ ጥያቄዎችና በተንፀባረቁ አስተያየቶች ላይም አቶ ደመቀ መኮንን ምላሽ እና ማብራሪያ እና የቀጣይ የስራ አቅጣጫም ላይም መመርያ መስጠታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል ።