ቀጥታ፡

በዱከም መውጫ በሚገኝ የጥጥ ፋብሪካ ላይ በደረሰ የእሳት አደጋ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት ወደመ

አዲስ አበባ(ኢዜአ) ታህሳስ 19/2015 በዱከም መውጫ በሚገኝ የጥጥ ፋብሪካ ላይ በደረሰ የእሳት አደጋ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት መውደሙን የአዲስ አበባ የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።

15 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት ማትረፍ መቻሉንም ገልጿል።

የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ቡድን መሪ አቶ ጉልላት ጌታነህ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ አደጋው ትናንት ከምሽቱ 1 ሰዓት ከ58 ደቂቃ ዱከም መውጫ ኢስት አፍሪካ ማዞሪያ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ በሚገኘው ንብረትነቱ ዶሪክ ከበደ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የጥጥ ፋብሪካ ላይ ነው።

በእሳት አደጋው 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት መውደሙንም አመልክተዋል።

የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ባደረጉት ርብርብ 15 ሚሊዮን የሚገመት ንብረት ማትረፍ እንደተቻለ ተናግረዋል።

ኮሚሽኑ እሳቱን ለማጥፋት 55 የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች እንዲሁም አምስት ከባድ እና ሁለት ቀላል የእሳት አደጋ መኪኖችን ማሰማራቱን ገልጸዋል።

በተጨማሪም የቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር ሁለት የአደጋ ጊዜ መኪናዎች እሳቱን ለማጥፋት ጥቅም ላይ መዋላቸውን ነው አቶ ጉልላት ያስረዱት።

እሳቱን ለማጥፋት ሶስት ሰዓት መፍጀቱንና የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች 30 ሺህ ሊትር ውሃ መጠቀማቸውን ተናግረዋል።

የኦሮሚያ ፖሊስ አባላት እሳት እንዲጠፋ ድጋፍ ማድረጋቸውንም አመልክተዋል።

የእሳት አደጋው መንስኤ አለመታወቁንና ፖሊስ በአደጋው ዙሪያ ምርምራ ማድረግ መጀመሩን ጠቁመዋል።

እንደ አቶ ጉልላት ገለጻ ከዚህ ቀደም በፋብሪካዎች የሚደርሱ አደጋዎች ዋንኛ መንስኤ የኤሌትሪክ ኃይል አጠቃቀም ችግር እና ተቀጣጣይ ነገሮች ናቸው።

ፋብሪካዎች የኤሌትሪክ ኃይል አጠቃቀማቸው ጥንቃቄ የተሞላበት ሊሆን እንደሚገባ ተናግረዋል።

ሕብረተሰቡ አደጋዎች ሲያጋጥሙ በነጻ የስልክ መስመር 939፤ በቀጥታ የስልክ መስመሮች 011 155 53 00 ወይም በ01 11 56 86 01 ደውሎ ማሳወቅ እንደሚችል አቶ ጉልላት ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም