በሐረሪ ክልል፣ ጅግጅጋ ከተማና ድሬደዋ አስተዳደር የሚገኙ 126 የፌደራል ተቋማት የመሬት ይዞታ ካርታ ተዘጋጅቷል

41

ታህሳስ 18 ቀን 2015 (ኢዜአ) በሐረሪ ክልል፣ ጅግጅጋ ከተማና ድሬደዋ አስተዳደር የሚገኙ 126 የፌደራል ተቋማት የመሬት ይዞታ ካርታ ማዘጋጀቱን የፌደራል መሬት ባንክና ልማት ኮርፖሬሽን ገለጸ፡፡

የፌደራል መሬት ባንክና ልማት ኮርፖሬሽን እና የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጂኦ-ስፓሻል ኢንስቲትዩት የተቋማቱን የይዞታ መሬት መረጃ አሰባሰብና ካርታ ሥራ በተመለከተ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

የመሬት ባንክና ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሌንሳ መኮንን እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ 4 ነጥብ 7 ሚሊየን ሄክታር የሚጠጋ የፌደራል ተቋማት የይዞታ መሬት በመረጃ ቋት ገብቷል፡፡

የይዞታ ልኬቱ ደረጃውን የጠበቀና ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ባለው መንገድ ለውሳኔ እንዲያመች ሆኖ መደራጀቱንም ገልጸዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥር ያሉ የፌደራል መንግሥት ተቋማትን ይዞታ ማጣራታቸውን የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፤ ከመጀመሪያው ልምድ በመውሰድ የሌሎች ክልሎችን መረጃ እናሰባስባለን ብለዋል፡፡

በሐረሪ ክልል72፣ በድሬደዋ 43 እና በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ 11 ተቋማት ላይ መረጃ በማሰባሰብ ካርታው ተዘጋጅቷል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጂኦ-ስፓሻል ኢንስቲትዩት የካርታ ሥራ መሪ ሥራ አስፈጻሚ ቴዎድሮስ ካሣሁን፤ በሐረሪ፣ ጅግጅጋና ድሬደዋ ያሉ 126 የፌደራል ተቋማት በይዞታቸው ላይ ያለውን ክፍት ቦታና ግንባታ አስመዝግበዋል ብለዋል፡፡

በዚህም የአየር ካርታ በመጠቀም በሐረሪ ክልል 72፣ ጅግጅጋ 11 እና ድሬደዋ 43 ተቋማት ላይ መረጃ በማሰባሰብ ካርታ ተዘጋጅቶላቸዋል ብለዋል፡፡

ካርታ የተዘጋጀላቸው 126ቱ የፌደራል ተቋማት 2 ሺህ 162 ሄክታር የቆዳ ስፋት የሚሸፍኑ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም