የተሻሻለው የኢትዮጵያ ሴቶች ጉዳይ ፖሊሲ በቅርቡ ወደ ስራ ይገባል

ደሴ ፤ ታህሳስ 18 ቀን 2015 (ኢዜአ) ፡- የተሻሻለው የኢትዮጵያ ሴቶች ጉዳይ ፖሊሲ በቅርቡ ፀድቆ ወደ ስራ እንደሚገባ የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

"ሴቶችን አከብራለሁ ጥቃታቸውንም እከላከላለሁ" በሚል መሪ ሀሳብ  የፀረ ፆታዊ ጥቃት ቀን  ለ17ኛ ጊዜ ዛሬ በደሴ ከተማ በፓናል ውይይት ተከብሯል።

ሚኒስቴሩ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በየደረጃው ግንዛቤ ከመፍጠር ባለፈ ጥቃቱን ለመከላከል፣  ጥቃቱ ሲፈጸምም እርምጃ ለመውሰድና ተጎጂዎች  እንዲያገግሙ ለመደገፍ  እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደም የነበረውን የኢትዮጵያ ሴቶች ፖሊሲ ማሻሻያ መጠናቀቁንና በቅርቡ በሚመለከተው አካል ፀድቆ ወደ ስራ እንደሚገባ ጠቁመዋል። 

የፖሊሲው መሻሻል በሴቶች ጥቃት ላይ ያለውን ችግር ያቃልላል ብለዋል ሚኒስትሯ።

ጥቃቱን ቀድሞ ከመከላከሉ በተጓዳኝ  ጥቃቱ ሲፈጸም ተጠቂዎች መልሰው የሚያገግሙበት፣ የስነ ልቦና ድጋፍ የሚያገኙበትና በኢኮኖሚም የሚቋቋሙበት የተሀድሶ ማዕከል ግንባታ በየክልሎች ለመገንባት ስራ መጀመሩን አስረድተዋል።

ለዚህም የችግሩን ስፋት ከግምት ውስጥ በማስገባት ማህበረሰቡ፣ተቋማት እና የሃይማኖት ተቋማት ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባም ተናግረዋል።

የአማራ ክልል ሴቶች ፣ሕጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ብርቱካን ሲሳይ፤  በሴቶች ላይ ጥቃት በሚፈጽሙ ግለሰቦች ላይ የሚወሰደው የሕግ እርምጃ ተመጣጣኝ አለመሆኑ ችግሩ እንዲባባስ ማድረጉን ገልጸዋል።

''ጥቃት ፈጻሚዎች ላይ አስተማሪ እርምጃ በመውሰድ ፍትህን ለማስፈን የድርሻችንን እንወጣለን'' ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል ፍትህ ቢሮ ሃላፊ አቶ ገረመው ገብረ ጻዲቅ ናቸው።

ጉዳዩ አሳሳቢ በመሆኑ ሁሉም የተደራጀ መረጃና ጥቆማ በመስጠት ሴቶችን ከጉዳት ለመታደግ በቅንጅት እንሰራለንም ብለዋል።

በአማራ ክልል ምክር ቤት የሕግና ፍትህ አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ወርቅነህ እንግዳ በበኩላቸው ፤ጥቃቱን ለመከላከል የሕግ ማዕቀፎች ጭምር እንዲስተካከሉና ተገቢ እርምጃ እንዲወሰድ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ችግሩን በክልሉ ዞኖችና ከተሞች ተዘዋውረው በመመልከት ግብረ መልስ ከመስጠት ባለፈ ህግ እንዲከበር ክትትልና ድጋፍ እየተደረገ ነው ብለዋል።

በፓናል ውይይቱ ላይ በፌዴራል ፣ክልልና ዞን ደረጃ የሚገኙ  የፍትህ፣ የፖሊስና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

ነባሩ የኢትዮጵያ ሴቶች ጉዳይ ፖሊሲ ከ1993 ዓ.ም አንስቶ ተግባራዊ በመሆን ላይ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም