በኢትዮጵያ እስካሁን 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዜጎች ዲጂታል መታወቂያ አግኝተዋል - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ እስካሁን 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዜጎች ዲጂታል መታወቂያ አግኝተዋል
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታሀሳስ 18/2015 በኢትዮጵያ እስካሁን 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዜጎች ዲጂታል መታወቂያ ማግኘታቸውን የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮጀክት አስታወቀ።
የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ ዮዳሄ ዘሚካኤል፤ የዲጂታል መታወቂያ አገልገሎት ባለፉት ሶስት አመታት የሙከራ ትግበራ ላይ መሆኑን ገልጸው በዚህም እስካሁን ለ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዜጎች የዲጂታል መታወቂያ መሰጠቱን ጠቅሰዋል።
የዲጂታል መታወቂያ ያገኙት የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ሲሆኑ የሴፍቲኔት መርሃ-ግብር ተጠቃሚዎች የዚሁ አገልገሎት ተጠቃሚ ሆነዋል ነው ያሉት።
አሰራሩ በግብርና ሚኒስቴር በኩል በሁሉም ክልሎች ተግባራዊ በሚደረገው የሴፍቲኔት መርሃ-ግብር ተጠቃሚ ዜጎችን በቀላሉ በመለየት ፍትሃዊ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አስችሏል ብለዋል።
የሴፍቲኔት መርሃ-ግብር አስተባባሪዎች አሰራራቸውን ከተጠቃሚዎች ዲጂታል መታወቂያው መለያ ቁጥር ጋር በማገናኘት እንዲሰሩ ማስቻሉንም አብራርተዋል።
በተመሳሳይ በሀዋሳና ቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ለሚሰሩ ሰራተኞች የዲጂታል መታወቂያ መሰጠቱን ገልጸዋል።
በአገር አቀፍ የፈተና አሰጣጥ ላይ እያንዳንዱ ተፈታኝ ልዩ የዲጂታል መታወቂያ ቁጥር የሚይዝበት አሰራር ስለመዘርጋቱም ጠቅሰዋል።
በዚህ አመት የዲጅታል መታወቂያ ተጠቃሚ ዜጎችን ቁጥር 12 ሚሊዮን ለመድረስ እቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የዲጂታል መታወቂያ ከተለያየ ቦታ የነዋሪነት መታወቂያ በማውጣት ይፈፀም የነበረውን ህገ ወጥነት የሚያስቀር መሆኑ ተመልክቷል።
የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮጀክት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ስር እየተተገበረ የሚገኝ ፕሮጀክት መሆኑ ይታወቃል።
የዲጂታል መታወቂያ ስርአትን በተመለከተ የተደነገጉ ተግባርና ሃላፊነቶችን የሚያስፈጽም ተቋምን ለማቋቋም የተዘጋጀው "የኢትዮጵያ ዲጅታል መታወቂያ ረቂቅ አዋጅ" ሲጸድቅ በአገር አቀፍ ደረጃ ስርአቱ የሚዘረጋ ይሆናል።