ቀጥታ፡

የአደጋ ስጋት ፍኖተ ካርታ አደጋዎችን አስቀድሞ በመከላከል ሰብአዊ ጉዳቶች እንዲቀንሱ የሚያደርግ ትልቅ እርምጃ ነው

አዲስ አበባ /ኢዜአ/ ታህሳስ 18/2015 በኢትዮጵያ የአደጋ ቅድመ ማስጠንቀቂያና ፈጣን ምላሽ አሰጣጥ ፍኖተ ካርታ "አደጋዎችን አስቀድሞ በመከላከል ሰብአዊ ጉዳቶች እንዲቀንሱ የሚያደርግ ትልቅ እርምጃ ነው" ሲል የዓለም ምግብ ፕሮግራም አስታወቀ።

የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ፍኖተ ካርታውን አስመልክቶ ያዘጋጀው የባለድርሻ አካላት ውይይት ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሄዷል።    

በአውደ ጥናቱ ላይ ፍኖተ ካርታውን ለማዘጋጀት በተከናወኑ ተግባራትና ጥቅሞቹ ላይ ማብራሪያ ተሰጥቷል።           

የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ዶክተር ሺፈራው ተክለማርያም፤ ፍኖተ ካርታው አደጋን አስቀድሞ ለመከላከል የሚረዱ ሀብቶችን የሚያሰባሰብ እና ሴክተር መስሪያ ቤቶች በቅንጅት የሚሰሩበትን አሰራር የያዘ መሆኑን ገልጸዋል።         

"በቅድመ ማስጠንቀቂያና ፈጣን ምላሽ አሰጣጥ ላይ ኢትዮጵያ የሚጠበቀው ደረጃ ላይ አልደረሰችም" ያሉት ኮሚሽነሩ በዚህ ረገድ ችግሮችን በማቃለል ፍኖተ ካርታው ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

የድርቅና የጎርፍ አደጋ በተደጋጋሚ የሚከሰትባቸውን ቦታዎች በመለየት ቅድመ መከላከል ላይ ለመስራት የሚያስችሉ ስልቶችን የያዘ መሆኑን ጠቅሰዋል።

እንደ አካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ ምላሽ የሚሰጥበት የተቀናጀ የአሰራር ስርዓት የሚዘረጋበት ነው ብለዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል አምባሳደር ዶክተር  የሺመብራት መርሻ በበኩላቸው ፍኖተ ካርታው ውጤታማ በሆነ መልኩ እንዲተገበር ድጋፍ እናደርጋለን ብለዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዓለም ምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ክላውዴ ጂቢዳር፤ ፍኖተ ካርታው አደጋዎችን አስቀድሞ በመከላከል ሰብአዊ ጉዳቶች እንዲቀንሱ የሚያደርግ ትልቅ እርምጃ ነው ብለዋል።  

ፍኖተ ካርታው ውጤት እንዲያመጣ ባሉን ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ በመስጠት አስፈላጊውን ድጋፍ እናደርጋለን ሲሉም አረጋግጠዋል።  

የአሜሪካ የልማት ተራድኦ ድርጅት(ዩኤስኤይድ) የኢትዮጵያ ተጠባባቂ ዳይሬክተር ቲም ስቴይን እንዳሉት፤ ድርጅቱ አደጋን መከላከል ላይ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ሲሰራ መቆየቱን አውስተዋል።

ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር አደጋን በመከላከል ዙሪያ በሺዎች ለሚቆጠሩ ተማሪዎች ስልጠና መስጠቱን አስታውሰው ፍኖተ ካርታው ውጤታማ እንዲሆን የሚጠበቅብንን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነን ሲሉም አክለዋል።

በፍኖተ ካርታው ውይይት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትና የክልሎች ተወካዮች ተገኝተዋል።

ፍኖተ ካርታው አደጋ ከመከሰቱ በፊት አስቀድሞ መከላከል ላይ ትኩረት ያደረገ ሲሆን የተቋማት ቅንጅት ምን መሆን እንዳለበት የሚያመላክት ነው ተብሏል።   

አደጋን አስቀድሞ ለመከላከል መረጃን ጥራት ባለው መንገድ ማሰባሰብ፣ መተንተን፣ መተንበይና ተግባራዊ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ማስቻል የፍኖተ ካርታው ዓላማ መሆኑም ተመልክቷል።   

ፍኖተ ካርታው ለሚቀጥሉት ስምንት ዓመታት ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን የልማት አጋሮች፣ የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽና ክልሎች በጋራ እንደሚተገብሩትም ተገልጿል።

ፍኖተ ካርታው በሁሉም በክልል፣ዞን እና ወረዳ ለአደጋ ፈጣን ምላሽ አሰጣጥ እንዲኖር የሚያግዝ ሲሆን ይህም ምላሽ አሰጣጡን ወደ ተሻለ ደረጃ እንደሚያሳድግ ታምኖበታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም