ለዘንድሮው የገና በዓል ከ15 ሺህ በላይ ሰንጋዎችን ለገበያ ለማቅረብ እየተዘጋጀ ያለው የሞረትና ጅሩ ወረዳ - ኢዜአ አማርኛ
ለዘንድሮው የገና በዓል ከ15 ሺህ በላይ ሰንጋዎችን ለገበያ ለማቅረብ እየተዘጋጀ ያለው የሞረትና ጅሩ ወረዳ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 18/2015 ለዘንድሮው የገና በዓል ከ15 ሺህ በላይ ሰንጋዎችን ለገበያ ለማቅረብ እየተዘጋጀ መሆኑን የሞረትና ጅሩ ወረዳ አስታወቀ።
በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የምትገኘው የሞረትና ጅሩ ወረዳ አርሶ አደሮች ከሰብል ልማታቸው ጎን ለጎን እንስሳትን አድልበው በመሸጥ፤ ጥምር ግብርናን የኑሮ ዘይቤ ካደረጉ ውለው አድረዋል።
በተለይም "የጅሩ ሰንጋ" የሚል አገራዊ የምርት መለያ ወይም 'ብራንድ' የተሰጠውና በአካባቢው አርሶ አደሮች ለገበያ የሚቀርበው ሰንጋ ተፈላጊነት እየጨመረ መምጣቱ ይገለጻል፡፡
በወረዳው ማንጉዶ ቀበሌ ነዋሪው አርሶ አደር አለማየሁ ሞላ በየዓመቱ በምግብና ጥራጥሬ ሰብል እንዲሁም በእንስሳት ልማት ላይ ባላቸው ተሳትፎ ሌማታቸው ከመሙላቱ ባሻገር፣ ተጨማሪ ገቢ በማመንጨት ኑሯቸው እንደተቃና ይመሰክራሉ።
የመኸር ሰብላቸውን እየወቁ ያገኘናቸው አርሶ አደር አለማየሁ ሞላ ላሞችን በማርባትም ከራሳቸው የወተት ተዋጽኦ ፍላጎት አልፈው ለገበያ ያቀርባሉ።
በወረዳው እንስሳት እርባታና መኖ ልማት ቡድን መሪ አቶ መዝገቡ ጌታቸው፤ የጅሩ አርሶ አደር እንስሳትን የማድለብ ባህል ብዙ ዓመታትን ያስቆጠረ ቢሆንም በጅሩ ሰንጋ በ2006 ዓ.ም ብራንድ ከተሰጠ በኋላ ምቹ የገበያ ትስስር ፈጥሯል።
ይህም እያንዳንዱ አርሶ አደር የበለጠ እንስሳት የማድለብ ተሳትፎ ውስጥ እንዲገባ ማድረጉን ገልጸዋል።
የወረዳው ግብርና ጽህፈት ቤትም በዝርያ ማሻሻል፣ በመኖ አቅርቦትና በእንስሳት ጤና ላይ ክትትልና ድጋፍ በማድረግ አርሶ አደሮች ውጤታማ እንዲሆኑ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
አርሶ አደሩ በእንስሳት ማድለብ ብቻም ሳይሆን በወተት ልማት፣ በዶሮ እና በንብ ማነብ በስፋት እንደሚሳተፉ ገልጸዋል።
በወረዳው በወተት ላም ዝርያ ማሻሻል በተሰራው ሥራም የወተት ምርታማነቱን በቀን ከ10 እስከ 15 ሊትር ማሳደግ እንደተቻለ አብራርተዋል።
በ2015 ዓ.ም ከ110 ሺህ በላይ የጅሩ ሰንጋዎችን ለገበያ ለማቅረብ ዕቅድ መያዙን ገልጸው፤ በተለይም አርሶ አደሩ የምርት መሰብሰብ ስራውን ካጠናቀቀ በኋላ በስፋት ወደ ማድለብ ሥራው ይገባል ነው ያሉት።
እስካሁን ባለው ሂደት በወረዳው ከ30 ሺህ በላይ የደለቡ ሰንጋዎች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ ለዘንድሮው የገና በዓል ከ15 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሰንጋዎች ለገበያ እንደሚቀርቡ ገልጸዋል።