በኢትዮጵያ የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ተደራሽነትን ለማሻሻል የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሰራር ሊጠናከር ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ተደራሽነትን ለማሻሻል የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሰራር ሊጠናከር ይገባል
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 18/2015 በኢትዮጵያ የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ተደራሽነትን ለማሻሻል ቅንጅታዊ አሰራርን እንዲጠናከር የጤና ሚኒስቴር ጥሪ አቀረበ፡፡
የጤና ሚኒስትር "የቤተሰብ እቅድ ፖሊሲ ከህዝብ እና ከእድገት አንጻር" በሚል መሪ ሃሳብ ከሚዲያ ተቋማት ባለሙያዎች ፤ከጤና ሚኒስቴር አመራሮች ፤ከክልል ጤና ቢሮ ኃላፊዎች ጋር ተወያይቷል፡፡
በውይይቱም የስነ-ተዋልዶ ጤና እና የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ተደራሽነት ፍትሃዊ ለሆነ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተገልጿል ፡፡
በጤና ሚኒስቴር የአገልግሎት እና ፕሮግራም ጽህፈት ቤት ኃላፊ ፍቃዱ ያደታ እንደገለጹት፤ አሁን ላይ በአገር አቀፍ ደረጃ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ተጠቃሚዎች ቁጥር 41 በመቶ እንዲሁም የወሊድ ምጣኔ 4 ነጥብ 2 በመቶ እንደደረሰ ተናግረዋል፡፡
በአገር አቀፍ ደረጃ በ2017 ዓ.ም የቤተሰብ ዕቅድ ተጠቃሚዎችን ከ41 በመቶ ወደ 50 በመቶ ከፍ ለማድረግ እየተሰራ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
ለዚህ አጋዥ የሆነና "ሼፕ 2 " የተሰኘ ፕሮጀክት ከኮሪያ የልማት ድርጅት ጋር በመተባበር በአምስት ክልሎች እና ሁለት መስተዳድሮች ተግባራዊ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
ፕሮጀክቱ በአማራ፤በኦሮሚያ ፣በሲዳማ ፣በደቡብ ፣በሶማሌ ክልሎችና እና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ተግባራዊ እንደሚደረግ ተገልጿል፡፡
በመሆኑም የቤተሰብ ዕቅድን አገልግሎት ተደራሽነት እንዲሻሻል የክልል ጤና ቢሮዎችን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሰራራቸውን ይበልጥ ማጠናከር እንዳለባቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በዓለም አቀፉ የህጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) የኢትዮጵያ ጤና ማዕከል የፕሮጀክት ተጠሪ ሴና በሊና በበኩላቸው፣ በኢትዮጵያ የሥነተዋልዶ ግንዛቤ ያላቸው ዜጎች ቁጥር ከፍተኛ ቢሆንም አተገባበሩ ላይ ክፍተት ይታያል ብለዋል፡፡
ከዚህ አኳያ በተለይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ተግባራት በስፋት ሊከናወኑ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡