ቅን ልቦና ለዘላቂ ሠላም

(በገዛኸኝ ደገፉ)

“ሰይፋቸውንም ማረሻ፣ ጦራቸውንም ማጭድ ለማድረግ ይቀጠቅጣሉ፤ ሕዝብም በሕዝብ ላይ ሰይፍ አያነሣም፣ ሰልፍም ከእንግዲህ ወዲህ አይማሩም።”

ይህ ትንቢት ከመጽሃፍ ቅዱስ ትንቢተ ኢሳይያስ ምዕራፍ 2 ቁጥር 4 ላይ ተወስዶ ኒውዮርክ በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና መሥሪያ ቤት ግድግዳ ላይ በጉልህ የሰፈረ አጭር ግን ደግሞ ጥልቅና ሰፊ ትርጉም ያለው ጥቅስ ነው።

የሁለተኛው የዓለም ጦርነት መጠናቀቅን ተከትሎ በጦርነቱ አሸናፊዎች ምስረታውን ያደረገው የመንግሥታቱ ድርጅት የዓለም ሰላም እና ደህንነት ማስጠበቅን ቀዳሚ መርህ አድርጎ ላለፉት 77 ዓመታት ሲሰራ ቆይቷል። ድርጅቱ ኒውዮርክ ከተማ በሚገኘው ዋና ጽህፈት ቤቱ ግድግዳ ላይ ማስፈሩም ለዓለም ሰላም እንዲበዛላት መሻቱን ያሳያል።

“ተ.መ.ድ የሠላም መሻቱ ምን ያህል እየተሳካለት ነው” የሚለው ለጊዜው እንለፈውና አሁንም በአገራት መካከል የሚከሰቱ አለመግባባቶችና ግጭቶችን ሠላማዊ እልባት እንዲያገኙ ብሎም በአገራት መካከል መልካም ወዳጅነት እንዲኖር እየሰራ ይገኛል። ያም ሆኖ በተለያዩ አገሮች መካከል አሊያም በአንድ አገር ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት አለመግባባቶች እየተፈጠሩ ወደ ግጭት ማምራታቸው ግን አሁን ድረስ ቀጥሏል።

ግጭትና መንስኤዎቹ

የተለያዩ መዛግብት እንደሚያስረዱት ግጭቶች በአስተሳሰብ ሂደት፣ በአመለካከት፣ በመረዳት፣ በዝንባሌዎች፣ በፍላጎቶች እና አንዳንዴም በግንዛቤ (Perceception) ልዩነቶች ምክንያት በግለሰቦች መካከል የሚፈጠሩ ቅራኔዎች ናቸው።

የግጭት መንስኤዎች በእርግጥ የበዙና የተለያዩ እንደሆኑ የሠላምና የግጭት አፈታት ምሁራን ያስረዳሉ። ግጭቶች የሚፈጠሩት ግለሰቦች የተለያየ እሴት፣ አስተያየት፣ ፍላጎት፣ ዝንባሌዎች እና አማካይ መቀራረብን ማግኘት በማይችሉበት ጊዜ እንደሆነም ይገልፃሉ። ግጭቶች የሚጀምሩት ግለሰቦች በተለያየ መስመር ሲያስቡ እና የሌላውን ሀሳብ ለመቀበል በጣም ሲቸገሩ ነው።

የግጭቶች መነሻ በርካታ ቢሆኑም የዘርፉ ምሁራን መንስኤዎቹን በዋናነት በሚከተለው መልኩ ከፍለው ያስቀምጡታል። አንደኛው የመረጃ ግጭቶች ሲሆን፤ ሰዎች የተለያየ ወይም በቂ ያልሆነ መረጃ ሲኖራቸው አሊያም በመረጃው ላይ አለመግባባት ሲፈጠር የሚከሰቱ ናቸው። የዚህ ዓይነት ግጭት እንዳይነሳ ለመደማመጥ በቂ ጊዜ መፍቀድ፣ አክብሮት በተሞላበት ሁኔታ ሁሉም ወገኖች የመረጃ ልዩነቶችን እንዲያጠሩ ማድረግ ይገባል።

ሁለተኛው መንስኤ የእሴቶች ግጭት ነው። ይህ ሰዎች የተገነዘቡት ወይም የማይጣጣሙ የእምነት ሥርዓቶች ሲኖራቸው የሚፈጠር ግጭት ነው። አንድ ሰው ወይም ቡድን እሴቶቹን በሌሎች ላይ ለመጫን ሲሞክር አሊያም የእሴቶቹን ስብስብ በብቸኝነት የማግኘት መብት ሲያነሳ በሚፈጠሩ ክርክሮች የሚነሳ ግጭት ነው። ያም ሆኖ እሴቶቹ ለድርድር የማይቀርቡ ሊሆኑ ቢችሉም ውይይት ሊደረግባቸው እና ሰዎች በሰላም እና በአንድነት አብረው መኖር የሚችሉበት ዕድል መፍጠር እንደሚችሉ መገንዘብ ይኖርባቸዋል።

ሦስተኛው መንስኤ የጥቅም ግጭት ሲሆን፤ የሚከሰተውም በሚታወቁ ወይም በተጨባጭ በማይጣጣሙ ፍላጎቶች ፉክክር ነው። እንዲህ ያሉ ግጭቶች በገንዘብ፣ በንብረት ወይም በኃብት ክፍፍል ጉዳዮች ሊከሰቱ ይችላሉ። አስታራቂ ፍላጎቶች ላይ ትኩረት በማድረግ ለጋራ ጥቅም ዕድሎችን መፍጠር ደግሞ ግጭቶች እንዳይከሰቱ ይረዳል።

ሌላው መንስኤ የግንኙነቶች ግጭት ነው። በዚህ ሳቢያ የሚከሰቱ ግጭቶች የተሳሳቱ አመለካከቶች፣ ጠንካራ አሉታዊ ስሜቶች ወይም ደካማ የሃሳብ ልውውጥ ሲኖር ነው። ይህም አንዱ በሌላው ላይ እምነት ሲያጣ እና የሌላው ድርጊት በክፋት ወይም ሌላውን ለመጉዳት በማሰብ ተነሳስቷል ከሚል እሳቤ የሚመነጭ ነው። የግንኙነቶች ግጭቶች እያንዳንዱ ሰው በችግሮቹ ውስጥ እንዲወያይ እና ለሌላው ሰው ስጋት ምላሽ እንዲሰጥ ጊዜ በመፍቀድ ሊፈታ ይችላል።

በመጨረሻም የግጭት መንስኤ ተደርጎ የተቀመጠው መዋቅራዊ ግጭት ነው። መዋቅራዊ ግጭቶች የሚከሰቱት ጨቋኝ ባህሪያት በሰዎች ላይ ሲጫኑ ነው። የውስን ኃብቶች እና ዕድሎች መኖር በአንድ በኩል ተቋማዊ መዋቅሮች በሌላ በኩል የግጭት ባህሪያትን ሲያበረታቱ ይስተዋላሉ። መዋቅራዊ ግጭትን ለመፍታት የኃይል ሚዛን መዛባትን ማመጣጠን የሚገባ ሲሆን፤ ሽምግልና (Mediation) ደግሞ ጠቃሚ መፍትሄ ተደርጎ ይወሰዳል።

የግጭት መንስኤ ምንም ይሁን ምን ተቀናቃኝ ወገኖች ትኩረታቸውን ከመጋጨትና ከመዋጋት ይልቅ ወደ መፍትሄ እንዲቀይሩ ውይይት እና ሰጥቶ መቀበልን የመጨረሻ አማራጭ አድረገው ሊወስዱ ይገባል።

የግጭቶች ተጽዕኖ

ግጭቶች በብሔራዊ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ልማት ላይ እንዴት ተጽዕኖ እንደሚያሳድሩ መረዳት አስፈላጊ ነው። ምክንያቱም ፖሊሲ አውጪዎች የግጭትን አፃፋዊ ተጽዕኖዎች ተረድተው ተጽዕኖውን ለመከላከል ውጤታማ ፖሊሲዎችን እንዲነድፉ የሚረዳ በመሆኑ።

የግጭቶች ቀጥተኛ ተጽዕኖዎች በእርግጥ ግልጽ ናቸው። ሞት እና የአካል ጉዳት፣ የህዝብ መፈናቀል፣ የንብረትና የመሰረተ ልማቶች መውደም እና የማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሥርዓቶች መቆራረጥ በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው። ግጭቶች የጦፈ ክርክርን፣ አካላዊ ጥቃትን እና የሰላም እና የስምምነት እጦትን ያስከትላሉ።

ግጭቶች ከሚፈጥሩት ሥነ-ልቦናዊና አዕምሯዊ ጫና ባለፈ ለብዙ አሥርት ዓመታት አልፎ ተርፎም ለትውልዶች የሚሻገር ከፍተኛ አሉታዊ ተጽእኖዎች ሊኖራቸው እንደሚችል ጥናቶች ያሳያሉ። በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ያልዳበረ ኢኮኖሚ ያላቸው አገሮች ምርታማነታቸውን በመቀነስ ዕድገታቸውን ያዳክማል፤ የድህነት ቅነሳ ጥረቱንም ሩቅ ያደርገዋል።

በረጅም ጊዜ ደግሞ ግጭቶች ግንኙነቶችን ሊለውጡ ይችላሉ። ለዘመናት በወዳጅነትና በመከባበር አብረው ይኖሩ የነበሩ ጓደኞች፣ ጎረቤቶች ወይም ህዝቦችን በግጭት ምክንያት ጠላት ሊሆኑ ይችላሉ፤ በተጨባጭም ሲሆኑ ታይቷል።

በዓለም ላይ የተከሰቱት ግጭቶች ሁሉ በጉልበት ይፈቱ ቢባል ከሰው ልጅ ልክየለሽ እልቂት ባለፈ በተፈጥሮ ሀብት ላይም ሊጠገን የማይችል ጉዳት ማስከተሉ አይቀሬ መሆኑ የሰላምና ደህንነት ምሁራን ይገልፃሉ። በቅርቡ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል እንዲሁም በሩሲያና ዩክሬን መካከል የተካሄዱት ግጭቶችና ጦርነቶችም ያስከተሉት ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት ይህንኑ ሃቅ የሚያረጋግጡ ናቸው።

ላለፉት ሁለት ዓመታት በሰሜን ኢትዮጵያ በተካሄደው ጦርነት ለደረሰው ውድመት መልሶ ለመገንባት 25 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር እንደሚያስፈልግ ሪፖሮቶች ያመላከታሉ። ይህን ያህል ከፍተኛ መጠን የሚጠይቀው የመልሶ ግንባታ ሥራ በኢትዮጵያ አቅም ብቻ ማከናወን ይቻላል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው።

የዓለም ማኅበረሰብ ትኩረቱን በዩክሬን ባደረገበት በአሁኑ ወቅት ምናልባት የዓለም ባንክና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ከሚያደረጉት መጠነኛ ድጋፍ ውጭ ሌላ አይጠበቅም።

እዚህ ላይ ባለፉት ሁለት ዓመታት በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የተካሄደው ጦርነት ካደረሰው ሁለንተናዊ ውድመትና ተጽዕኖ ግንዛቤ በመውሰድ መሰል ጥፋት በሌሎች የአገሪቷ ክፍሎች እንዳይደገም በሁሉም ዘንድ ማስተዋል ይገባል።

እርቀ ሠላም በኢትዮጵያ

ከአራት ዓመት በፊት በኢትዮጵያ የታየው ለውጥ ከግለሰቦች እስከ ፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሁም ከክልሎች እስከ ፌዴራል መንግሥት የደረሰ አለመግባባቶችን ፈጥሯል። መንስኤዎቹ ምን ይሁን ምን አለመግባባቶቹ ወደ ግጭት አምርተው ለሁለት ዓመታት የዘለቀ ደም አፋሳሽ ጦርነት እንዲካሄድ ምክንያት ሆነዋል።

ቀደም ሲል ይታዩ የነበሩ አለመግባባቶች ተካረው ወደ ግጭት ከማምራታቸው አስቀድሞ የኢትዮጵያ መንግሥት ችግሩን በንግግር እና በውይይት እንዲፈቱ ከፍላጎት ባለፈ አገር በቀል የግጭት አወጋገድ ሥርዓትን ጨምሮ ሌሎች የሰላም ማስገኛ ጥረቶችን ገቢራዊ ሲያደርግ ቆይቷል፤ አሁንም እያደረገ ይገኛል። ደቡብ አፍሪካ ከመሰሉ በመስኩ ጠቃሚ ልምድ ካላቸው አገሮች ተሞክሮ በመውሰድ በመጀመሪያ የዕርቀ ሰላም ኮሚሽን ቀጥሎም የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአዋጅ ቁጥር 1265/2014 አቋቁሞ ወደ ሥራ ከገባ ሦስት ዓመት አስቆጥሯል።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ለገባችበት የሠላም እጦትና የተወሳሰበ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ምስቅልቅል ሁነኛ የመፍትሔ መንገድ ተብሎ የሚታሰበው በረጅም ጊዜ ነገር ግን በመተማመን ውስጥ የሚደረግ እውነተኛና አካታች አገራዊ ምክክር ነው። የተመሰረተው አገራዊ የምክክር ኮሚሽን በኢትዮጵያ ሥር የሰደዱ ቁርሾዎችን እና አለመግባባቶችን እንዲሁም አካባቢያዊ ግጭቶችን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት የሚያገለግል ሁነኛ የግጭት መፍቻ እንደሚሆን ተስፋ ተጥሎበታል።

ለሰው ልጆች እና ለምድሪቷ ሠላም ሲባል ተፋላሚ ኃይሎች መሳሪያቸውን አስቀምጠው ለንግግርና ውይይት ራሳቸውን ከማስገዛት ባለፈ ሰጥቶ መቀበልን መለማመድ ይኖርባቸዋል። ሰጥቶ መቀበል ከሚተገበርባቸው መንገዶች መካከልም ብሔራዊና ሁሉን አቀፍ ምክክሮች ማካሄድ እንደሆነ ኤልዛቤት ሙሪ እና ሱዛን ስቲጋንት የተባሉ የሠላም ተመራማሪዎች በፈረንጆቹ አቆጣጠር 2015 በአሜሪካ የሠላም ተቋም የድረ-ገጽ መጽሄት ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ በስፋት አብራርተዉታል።

‹‹ብሔራዊ የውይይትና የድርድር መድረኮችን ወደ ብጥብጥና ግጭቶች የሚመሩ መንገዶችን በመለየት አካታች የመፍትሔ አማራጭ ሃሳቦች የሚገኙበት ነው›› የሚሉት ምሁራኑ ጥቃቅን ምክንያቶች የግጭቶች መነሻ ሊሆኑ እንደሚችሉ ሁሉ ጥቃቅን ጉዳዮችም የሠላም አማራጭን ሊያመላክቱ ስለሚችሉ ንግግሮች ከታችኛው ማኅበረሰብ ሊጀመሩ ይገባል ባይ ናቸው፡፡ ግጭትን ለማስወገድ እና ሠላምን ለመገንባት ደግሞ አገራዊ ምክክር ሁነኛ አማራጭ መሆኑን ያስምሩበታል።

አገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ሁሉን አቀፍና አካታች አገራዊ ምክክርን በስፋት ያካሂዳል ተብሎ ይጠበቃል። ይህ ደግሞ እነ ኤልዛቤት ሙሪ እና ሱዛን ስቲጋንት ከሚያነሱት ሃሳብ ጋር የሚጣጣም ሆኖ እናገኘዋለን። የሚደረገው አገራዊ ምክክር በተለመደው የስብሰባ ዓይነት አንድ ሀሳብ እና የተወሰነ ወገን ብቻ ተገናኝቶ የሚመክርበት አካሄድ ሳይሆን “የኅብረተሰቡ የልብ ትርታዎች ናቸው” የተባሉ ሃሳቦች፣ ቅሬታዎች፣ ጥቅሞች፣ ምኞቶች፣ ፍላጎቶችና መብቶች የሚንጸባረቁበት እንደሚሆን ይጠበቃል።

የትኩረት ጉዳዮች

ሃገራዊ የዕርቀ ሠላም ኮሚሽን ግጭቶችን ለመፍታት፣ ጉልህ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለማጣራት፣ የሽግግር ፍትሕ ለመስጠት፣ የሕዝቡን አብሮነት የሚያጠናክሩ ተግባራትን ለማከናወን እና ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር የሚያስችሉ ሥራዎች ላይ ትኩረት አድርጌያለሁ ማለቱ ይታወቃል።

በተጨማሪም በኢትዮጵያ የሚስተዋሉ ሥር የሰደዱና መሰረታዊ የሠላም እጦትና ልዩነቶች በኅብረተሰቡ ሙሉ ተሳትፎ መፍትሄ እንዲያገኙ የሚያስችሉ ሥራዎችም እንደሚሰራ አመልክቷል። ነገር ግን ህዝባዊ ውይይቶች በሚያደርግበት ወቅት (ይህን ይሰተዋል ተብሎ ባይጠበቅም) ኮሚሽኑ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራባቸው የሚገባቸው ጉዳዮች እንዳሉ ማመላከትና ማስታወስ ተገቢ ይሆናል።

አገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም፣ በተለይም መገናኛ ብዙሃንን በአግባቡ ስራቸወን እነዲያከናውኑ በማድረግና ትምህርታዊ ዝገጀቶችነ በማቅረብ በህብረተሰቡ ዘንድ ሊያከናውናቸው የሚገቡ መሰረታዊ ጉዳዮችን መጥቀስ እወዳለሁ።  

የመጀመሪያው ህብረተሰቡ ስለምክክሩ አዎንታዊ አመለካከት (Positive Attitude) እንዲይዝ የሚያደርጉ ስራዎችን በስፋት ማካሄድ ተገቢ ነው። ግጭቶችን በዘላቂነት ለማስወገድ አዎንታዊ አመለካከት ወሳኝ ነው። በምክክር ጊዜ መቃወምን ማስወገድ ግንኙነት እንዳይበላሽ የሚረዳ ይሆናል።  የሚነሱ ሀሳቦችን በቀናነት በመመልከት በመጠያየቅና በመረጃ ላይ መሰረት ባደረገ መልኩ ሃሳብን በመግለጽ መቃወምን ማስወገድ ለአዎንታዊ አመለካካት መጎልበት የራሱ መልካም አስተዋጽኦ ይኖረዋል። ይህ ደግሞ ይበልጥ መተማመንን የሚፈጥር በመሆኑ ለሂደቱ መሳካት ጠቃሚነቱ ቀላል አይሆንም።

ግትር አስተሳሰቦችን ችላ ማለት (Ignoring Stuborn Views) ሌላው ሊተኮርበት የሚገባው ጉዳይ ነው። ግለሰቦች የአንዱን አሊያም የሁሉንም ፍላጎት ያገናዘበ የመካከለኛው መንገድ አካሄድን ለመቀበል መሞከር ይኖርባቸዋል። በጣም ግትር ለሆነ እና ለመግባባት ዝግጁ ላልሆነ ሰው ጊዜና ጉልበት ያለአግባብ ማባከን አያስፈልግም። በጣም ብዙ ፍላጎቶች የሚያንጸባርቅን ሰው ችላ ማለትም ይገባል። ይህ ደግሞ ችግሩን ለማወሳሰብ የሚደረጉ ጥረቶችን በግማሽ ያህል ለመፍታት የሚረዳ ይሆናል።

ነቀፌታን ማስወገድ (Never Criticize) ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። የሰዎችን ፍጹም አለመሆንን ታሳቢ በማድረግ የተሳሳተ ሃሳብ ተንጸባርቆ እንደሆነ ግለሰቡ እንዲረዳ ማድረግ እንጂ መንቀፍ አይገባም።

በጥቅሉ ዴሞክራሲያዊት እና እኩልነት የነገሰባት ኢትዮጵያ እውን የማድረግ ዕጣ ፈንታ በይቅርታ፣ በእውነትና በእርቅ፣ በአዲስ መንፈስና ርዕይ ተፈቃቅዶ በአንድነት መጓዝ ሲቻል ነው።

በብዙ ምስቅልቅሎች ውስጥ ያለፈው የኢትዮጵያ ህዝብም በሠላምና በትብብር ተከባብሮ ሊኖር የሚችለው ተፈጽመዋል የሚላቸውን ጥፋትና በደሎች በአደባባይ በይፋ ሲናገርና አስፈላጊ የሆነ ምክክር ሲደረግበት ነው። “በእነዚህ ወቅቶች ተፈጽመዋል” የተባሉ ወንጀሎችና ጥፋቶች ተገቢውን እውቅና አግኝተው ለዛሬውም ሆነ ለመጭው ትውልድ መማሪያ እንዲሆኑ ሲደረግ ነው። በሂደቱ ያለፉ የሌሎች አገሮች ልምድም የሚያሳየን ከዚህ የተለየ አይደለም።

ዓለም የቅርብ ጊዜ የጅምላ ፍጅት ማሳያ አድርጎ የሚያቀርባት ትንሿ አፍሪካዊት አገር ሩዋንዳም በ1990ዎቹ ያለፈችበትን የእርስ በእርስ ጦርነት ያስከተለው የዘር ፍጅት ዘመናዊውን የሕግ ሥርዓት ከባህላዊው የጋካካ (Gacaca) የግጭት አፈታትና የይቅርታ ዘይቤ ጋር በማዛመድ እውነትና እርቅን በማፈላለግ በአገሪቷ ሰላም ማስፈን ችላለች።

በደቡብ አፍሪካ በተደረገው የሠላም እና እውነትን የማፈላለግ ሂደት “በሺዎች የሚገመቱ ተጎጂዎች፣ የተጎጂ ቤተሰቦችና ወንጀለኞች ናቸው” የተባሉ ግለሰቦች ለሂደቱ “ቃላቸውን በመስጠት ጥፋታቸውን በማመን” ሃገራቸውንና ህዝባቸውን ከቀጣይ መበቃቀልና የፍጅት አዙሪት እንድትወጣ ማድረግ ችለዋል። ኢትዮጵያውያንም ይህን ማድረግ የማይችሉበት አንዳች ምክንያት ሊኖር አይችልም።

ግጭት የትም እንደማያደርስ በግል መገንዘብ ይገባል። የእርስ በርስ ግጭት እና መናቆር ወደ ሠላማዊ መደምደሚያ ፈጽሞ አያደርሱም። ስለዚህ ዜጎች በሰከነ መንፈስና በቅን ልቦና በጋራ መክረው ሠላማቸውን ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል። ለዚህ ደግሞ አገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ በሚያዘጋጃቸው የምክክር መድረኮች በንቃት በመሳተፍ የመፍትሄው አካል የመሆን ዕድሉን መጠቀም ይገባል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም