የቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ የንግስ በዓል ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲከበር አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል- ፌዴራል ፖሊስ - ኢዜአ አማርኛ
የቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ የንግስ በዓል ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲከበር አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል- ፌዴራል ፖሊስ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 18/2015 የቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ የንግስ በዓል ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲከበር አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ገለጸ፡፡
ህብረተሰቡ ስጋት ሊሆኑ የሚችሉ አጠራጣሪ ነገሮችን ሲመለከት በአቅራቢያው ለሚገኙ የጸጥታ አካላት ጥቆማ እንዲሰጥም ፌዴራል ፖሊስ ጥሪ አቅርቧል።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የንግስ በዓሉ በሰላም እንዲከበር ፖሊስ ቀደም ብሎ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡
በዚህም የፌዴራል ፖሊስ ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አመራሮች ጋር ውይይት ማድረጉን አስታውስዋል።
በበርካታ የእምነቱ ተከታዮች ዘንድ በዓሉ በድምቅት በሚከበርባቸው አካባቢዎች ፌዴራል ፖሊስ ከሌሎች የጸጥታ ተቋማት ጋር በመቀናጀት አስፈላጊውን የጸጥታ ጥበቃ ስራ መሰራት የሚያስችለውን ዝግጅት አድርጓል ነው ያሉት፡፡
ከዚህ አኳያ በቁልቢ የሚከበረው በዓል ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲከበር ፌዴራል ፖሊስ፣ ከኦሮሚያ፣ ከሐረሪና ድሬደዋ ፖሊስ ኮሚሽኖች ጋር በመቀናጀት የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን ማከናወኑን ጠቅሰዋል፡፡
በሐዋሳ የሚከበረውን በዓል በሚመለከትም የፌዴራል ፖሊስ ከሲዳማ እንዲሁም ከደቡብ፣ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልሎች ፖሊስ ኮሚሽኖች ጋር በመሆን አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አገራዊ ለውጡን ተከትሎ ባከናወናቸው የሪፎርም ስራዎች ህዝባዊና ሃይማኖታዊ በዓላት በሰላም እንዲከበሩ በቴክኖሎጂ የታገዘ ጥበቃ እያደረገ መሆኑን አስታውስዋል።
በመሆኑም የቴክኖሎጂ አቅሞችን በመጠቀም ጭምር የቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ የንግስ በዓል ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲከበር በቂ ዝግጅት ተደርጓል ነው ያሉት።
ኀብረተሰቡ የጸጥታ ስጋት ሊሆኑ የሚችሉ አጠራጣሪ ነገሮችን ሲመለከት በአቅራቢያው ለሚገኙ የጸጥታ አካላት ጥቆማ መስጠት እንዳለበትም ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፈንታ ጥሪ አቅርበዋል፡፡