በምሥራቅ ጎጃም ዞን በበጋ መስኖ ስንዴ ለማልማት ከታቀደው 11 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር ተሸፍኗል - ኢዜአ አማርኛ
በምሥራቅ ጎጃም ዞን በበጋ መስኖ ስንዴ ለማልማት ከታቀደው 11 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር ተሸፍኗል
ደብረ ማርቆስ (ኢዜአ) ታህሳስ 18/2015 በምስራቅ ጎጃም ዞን በበጋ መስኖ ስንዴ ለማልማት ከታቀደው 20 ሺህ 500 ሄክታር መሬት 11 ሺህ ሄክታሩ በዘር መሸፈኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ ገለጸ።
በዞኑ እነማይ ወረዳ በተለያዩ ቀበሌዎች አርሶ አደሩን የሚያበረታታ የመስኖ ሳምንት የንቅናቄ መድረክ ተካሄዷል።
የመምሪያው ሃላፊ አቶ ፈንታሁን ቸኮል እንዳሉት፣ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በአርሶ አደሩ ዘንድ ያልተለመደ ቢሆንም በልማቱ እንዲሳተፍ በንቅናቄ ጭምር ድጋፍ በመደረጉ ለውጥ እየታየ ነው።
በተያዘው የበጋ ወቅት በዞኑ 20 ሺህ 500 ሄክታር መሬት ላይ ስንዴ በመስኖ ለማልማት ታቅዶ ወደ ሥራ የተገባ ሲሆን እስካሁን ከ11 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለምቷል ብለዋል።
አቶ ፈንታሁን እንዳሉት በዞኑ በበጋ መስኖ በዘር ከሚሸፈነው መሬት ከ922 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ሲጠበቅ ከእዚህ ወስጥ 195 ሺህ ኩንታሉ ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ነው።
"ዕቅዱን ለማሳካት በቂ ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ እየቀረበ ነው" ያሉት መምሪያ ሃላፊው፣ ለልማቱ 6ሺህ የውሃ መሳቢያ ጀነሬተሮች በግልና በቡድን ተደራሽ መደረጋቸውንም ተናግረዋል።
የምስራቅ ጎጃም ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ መንበሩ ዘወዴ በበኩላቸው የመስኖ ስንዴ ልማቱ ከአርሶ አደሩ እና ከግብርና ባለሙያዎች ጋር መግባባት ተደረሶ ከገጸ ምድር ውሃ በተጨማሪ የከርሰ ምድር ውሃን በመጠቀም እንዲከናወን እየተደረገ ነው ብለዋል።
ለልማቱ ስኬታማነት በየደረጃው ያለ አመራር እና ባለሙያ ድጋፍና ክትትል እያደረገ መሆኑን የጠቆሙት አቶ መንበሩ፣ ለአርሶ አደሩ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።
በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በመሳተፍ ምርታማነታቸውን ለማሳደግ ከግማሽ ሄክታር በላይ ማልማታቸውን የገለጹት ደግሞ በእነማይ ወረዳ የማህበረ ብርሃን ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ማናየ ተስፋው ናቸው።
በቀጣይ የበለጠ ተጠቃሚ ለመሆን የተሻሻሉ የግብርና አሰራሮችን በመተግበርና በልምድ በመታገዝ ልማቱን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
በዞኑ ባለፈው ዓመት በተካሄደ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት 4ሺህ ሄክታር መሬት በማልማት 140 ሺህ ኩንታል ምርት መገኘቱ ታውቋል።