ቀጥታ፡

በሰሜን ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት በሚደረገው እንቅስቃሴ የመንግስት ጥረት የሚደነቅ ነው- የጃፓን አምባሳደር ኢቶ ታካኮ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 18/2015 በሰሜን ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት በሚደረገው እንቅስቃሴ የመንግስት ጥረት የሚደነቅ መሆኑን በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ኢቶ ታካኮ ገለጹ።

የጃፓን መንግስት ለሰላም ስምምነቱ ተግባራዊነትና ዘላቂ ሰላም የበኩሉን እገዛ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ኢቶ ታካኮ በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በመንግስትና በህወሃት መካከል ለሁለት ዓመት የዘለቀው ግጭት እልባት እንዲያገኝ የተደረሰው የሰላም ስምምነት ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ልዩ ትርጉም የሚሰጠው ነው።

የፌዴራል መንግስት ለሰላም ስምምነቱ ተፈጻሚነቱ እያሳየ ያለው ሚና አስደናቂ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ መሪነት ወደ መቀሌ የተደረገው ጉዞ የሰላም ስምምነቱን ተፈጻሚ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት የመንግስት ቁርጠኝነት በተግባር የታየበት ትልቅ ርምጃ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ሰላም መሆን ከህዝቦቿ ባለፈ ለቀጠናው ሀገራት ጭምር ጠቃሚ መሆኑን ያነሱት አምባሳደሯ መንግስታቸው ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ሁለቱ ወገኖች የያዙትን ቁርጠኝነት የጃፓን መንንግስት ያደንቃል ብለዋል።

የጃፓን መንግስት ለሰላም ስምምነቱ ተግባራዊነትና ዘላቂ ሰላም የበኩሉን እገዛ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

መንግስታቸው ለሰላም ትግበራው ተፈጻሚነት ድጋፍ እንደሚያደርግ በማንሳት፣ አሁን ላይ በሰሜን ኢትዮጵያ የሰብዓዊ ድጋፎችን እያደረጉ መሆኑን አንስተዋል።

በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ሀገራዊ ምክክርን ጨምሮ የሰላም ጥረቶች ስኬታማ እንዲሆኑ ጃፓን ድጋፍ ታደርጋለች ብለዋል።

የጃፓን መንግስት ለሰላም ስምምነቱ ተግባራዊነት ማገዝ የሚችልባቸውን ጉዳዮች የመለየት ስራ እያከናወነ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም