ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ የአራተኛ ሳምንት መርሐግብር የባህር ዳር ከነማ እና ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ በአቻ ውጤት ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ(ኢዜአ) ታህሳስ 18/2015 በኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ የባህር ዳር ከነማ እና ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ጨዋታ 35 ለ 35 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቀቀ ።

የፕሪሚየር ሊጉ የአራተኛ ሳምንት መርሐግብር የመጨረሻ ጨዋታ ዛሬ በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ተካሄዷል።

በባህርዳር ከነማ እና በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ መካከል በተካሄደ ጨዋታ 35 እኩል በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

በጨዋታው ተመጣጣኝ እና ጠንካራ ፉክክር ለማየት ተችሏል።

በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ከአንደኛ እስከ አራተኛ ሳምንት ሲካሄድ የነበረው የሊጉ መርሐግብር ዛሬ ተጠናቋል።

ቀጣይ የፕሪሚየር ሊጉ ጨዋታዎች ከጥር 16 እስከ የካቲት 2 ቀን 2015 ዓ.ም በድሬዳዋ እንደሚካሄዱ የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።

በሌላ በኩል የድሬዳዋ ከተማ ክለብ በመወዳደሪያ ሕጉ መሰረት በሁለት ተከታታይ ጨዋታ ሜዳ ላይ ባለመገኘቱ ከውድድሩ እንዲሰረዝ መደረጉን ገልጿል።

የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ በስምንት ነጥብ ይመራል። መቻል በስድስት ነጥብ ይከተላል።

ኦሜድላ እና ባህር ዳር ከነማ በተመሳሳይ አራት ነጥብ በግብ ልዩነት ተበላልጠው ሶስተኛ እና አራተኛ ደረጃን ይዘዋል።

በፕሪሚየር ሊጉ ያደረጋቸውን አራት ጨዋታዎች የተሸነፈው ሚዛን አማን ከተማ ያለ ምንም ነጥብ የመጨረሻውን ዘጠነኛ ደረጃ ይዟል።

በኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን የውድድር መመሪያ መሰረት አንድ ቡድን ሲያሸንፍ ሁለት አቻ ሲወጣ አንድ ነጥብ ያገኛል

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም