በአዲስ አበባ ከተማ የብዝሀ ቋንቋ አተገባበር ዙርያ በተካሔደ የጥናት ውጤት ላይ ውይይት ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ ከተማ የብዝሀ ቋንቋ አተገባበር ዙርያ በተካሔደ የጥናት ውጤት ላይ ውይይት ተደረገ

አዲስ አበባ ታህሳስ 18/2015፦የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች ለብዝሀ ቋንቋ አተገባበር እና ከአፍ መፍቻ በተጨማሪ የሀገር ውስጥና የውጪ ቋንቋዎችን በስርዓተ ትምህርት ለማካተት በተካሄደ ጥናት ውጤት ዙሪያ ተወያዩ።
ውይይቱ የተካሄደው የከተማ አስተዳደሩ ከኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ጋር ባደረገው የጥናት ውጤት ላይ መሆኑ ተነግሯል።
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ጥናቱ ከባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ጀምሮ ሲደረግ መቆየቱን ጠቅሰው በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በውይይት እየዳበረ መሆኑን አስረድተው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮችም በግልፀኝነት ተወያይተውበት በቀጣይ ህዝቡን ማወያየት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል::

የጥናት ፅሁፉን ያቀረቡት የኮተቤ ዩኒቨርሲቲ መምህር ዶክተር ዮሴፍ ከአንድ በላይ ቋንቋዎችን ማወቅ ከሚያስገኘው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ በተጨማሪ ማህበራዊ መስተጋብርንና ትስስርን የማጠናከር እና ሌሎች ፍልስፍናዊና ባህላዊ እውቀቶችን የሚያጎናጽፍ ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያም በተለይም ኦሮሚያ ክልል ከሌሎች ክልሎች ጋር በሚዋሰንባቸው አካባቢዎችና በሌሎችም ክልሎች የተጀማመሩ ስራዎች ያስገኟቸውን መልካም ውጤቶች በመጥቀስ ማብራራታቸውን ከከተማዋ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
በተደረገው ጥናት ከአገር ውስጥ ቋንቋዎችና ከእንግሊዝኛ በተጨማሪ ከቅርበት ከተደራሽነት እና በሌሎች ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ምክንያቶች ሌሎች የአካባቢው ቋንቋዎችንም ለመማር ምርጫቸው መሆኑ በጥናቱ መረጋገጡ ቀርቧል።
ጥናቱ የተማሪዎችን፣ የመምህራንንና የወላጆችን ሀሳብ በማካተት ለምሁራን ቀርቦ በተጨማሪ ግብዓት የዳበረና በቀጣይም የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችም በውይይታቸው የበለጠ የሚያዳብሩት መሆኑ ተገልጿል።
በውይይቱ የተሳተፉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አመራሮችም ለብዝሀ ቋንቋ አተገባበር ከአፍ መፍቻ በተጨማሪ የሀገር ውስጥና የውጪ ቋንቋዎችን መማር የጥናት ውጤትም መሬት ላይ ያለውን እውነታ ያረጋገጠ መሆኑንና የቀጣዩ ትውልድ ማህበራዊ ትስስርን የበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የጎላ ፋይዳ እንዳለው አስረድተዋል።