ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዳግም ወደ መቀሌ በረራ መጀመር የሰላም ሒደቱን ያጠናክራል

አዲስ አበባ /ኢዜአ/ ታህሳስ 18/2015፦ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዳግም ወደ መቀሌ በረራ መጀመር የሰላም ሒደቱን እንደሚያጠናክረው የአየር መንገዱ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ገለጹ።

አየር መንገዱ በነገው እለት መደበኛ በረራውን ዳግም እንደሚጀምር አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ዛሬ በሰጡት መግለጫ ከአየር መንገዱና ከኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን የተወጣጣ የባለሙያዎች ቡድን በመቀሌ አውሮፕላን ማረፊያ ተዘዋውሮ ጉብኝት ማድረጉን ገልጸዋል።

በዚህም ቡድኑ አውሮፕላን ማረፊያው ለበረራ ዝግጁ መሆኑን ማረጋገጡን ጠቅሰው፤ ከነገ ጀምሮ መደበኛ የመንገደኞች በረራ እንደሚጀምር ገልጸዋል።

መደበኛ በረራው በቀን አንድ ጊዜ የሚደረግና በሂደት እየጨመረ እንደሚሄድም ጨምረው ገልጸዋል።

አየር መንገዱ ዳግም በረራ መጀመሩ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን በማጎልበት የሰላም ሂደቱን እንደሚያጠናክር ተናግረዋል፡፡

የትግራይ ክልል በኢትዮጵያ የቱሪስት መዳረሻ ከሆኑ ስፍራዎች መካከል እንዷ መሆኗን ያስታወሱት ዋና ስራ አስፈጻሚው፤ ዳግም በረራ መጀመሩ ተቀዛቅዞ የቆየውን የቱሪዝም ዘርፍ ለማነቃቃት በጎ ሚና እንደሚኖረውም አንስተዋል፡፡

በክልሉ እየተከናወነ ያለውን ሰብዓዊ ድጋፍ ለማሳለጥ እንደሚያግዝም እንዲሁ፡፡

አየር መንገዱ በክልሉ ወደሚገኙ ሌሎች አውሮፕላን ማረፊያዎች በቅርቡ በረራ እንደሚጀመርም ተናግረዋል፡፡

ከጥቂት ሳምንታት በፊት አየር መንገዱ ዳግም ወደ ትግራይ ክልል በረራ ለመጀመር በዝግጅት ላይ መሆኑን ለኢዜአ መግለጹ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም