ኢትዮጵያ የውስጥ ችግሮቿን በሰላማዊ አማራጭ ለመፍታት እያከናወነች ያለውን ጥረት ለማስተዋወቅ በትኩረት እንሰራለን- አምባሳደሮች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የውስጥ ችግሮቿን በሰላማዊ አማራጭ ለመፍታት እያከናወነች ያለውን ጥረት ለማስተዋወቅ በትኩረት እንሰራለን- አምባሳደሮች
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 18/2015 ኢትዮጵያ የሰላም ስምምነቱን ጨምሮ የውስጥ ችግሮቿን በሰላማዊ አማራጭ ለመፍታት እያከናወነች ያለውን ጥረት በማስተዋወቅ ረገድ በትኩረት እንደሚሰሩ በተለያዩ አገራት ኢትዮጵያን የወከሉ አምባሳደሮች ተናገሩ፡፡
ዓመታዊ የአምባሳደሮች ጉባዔና ሥልጠና በአፍሪካ የአመራር ልህቀት አካዳሚ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
በጉባዔው ላይ እየተሳተፉ ከሚገኙት ዲፕሎማቶች መካከል በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ፣ በኳታር የኢትዮጵያ አምባሳደር ፈይሰል ዓሊ እና በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ፤ ኢትዮጵያና ቻይና ከግማሽ ምዕተ-ዓመት በላይ ያስቆጠረ ጠንካራ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ያላቸው አገሮች መሆናቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያና ቻይና በትብብርና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ የቆየ ወዳጅነት እንዳላቸው ጠቅሰው፤ አሁንም ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።
በተለይ ከሁለትዮሽ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱ ባሻገር ቻይና በባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች ከኢትዮጵያ ጎን በመቆም አጋርነቷን አሳይታለች ብለዋል።
በኳታር የኢትዮጵያ አምባሳደር ፈይሰል ዓሊ፤ የጋራ ተጠቃሚነትን መሠረት ያደረገው የኢትዮጵያና ኳታር ግንኙነት ሰፊ የኢንቨስትመንት ዕድሎችን የያዘ ስለመሆኑ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያና ኳታር የጋራ ተጠቃሚነትንና ሉዓላዊነትን ባከበረ መልኩ የተሳሰረ ግንኙነት መሆኑንም አብራርተዋል።
በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያና ፓኪስታን የሁለትዮሽ ግንኙነትን በማጠናከር ቀጣናዊና ዘርፈ-ብዙ ትብብር እንዳላቸው ገልጸዋል።
ፓኪስታን በተለያዩ ጊዜያት በኢትዮጵያ ላይ የሚደረጉ ተፅዕኖዎችን በመቃወም አጋርነት ማሳየቷን ገልጸው፤ የሁለቱን ሀገራት የሁለትዮሽ፣ ቀጣናዊና ባለብዙ ወገን ግንኙነት በመልካም ደረጃ ያለ እና ይህንኑም የበለጠ ለማሳደግ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረውን ችግር በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት በአፍሪካ ሕብረት ጥላ ሥር ለተደረገው የሰላም ስምምነት ቻይና፣ ኳታርና ፓኪስታን ማድነቃቸውን አምባሳደሮቹ ገልጸዋል።
የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ ለመልሶ ግንባታና ማቋቋም ቻይና፣ ኳታርና ፓኪስታን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ማረጋገጣቸውን በየአገራቱ የኢትዮጵያ አምባሳደሮች ገልጸዋል።
በመሆኑም ኢትዮጵያ የሰላም ስምምነቱን ጨምሮ የውስጥ ችግሮቿን በሰላማዊ አማራጭ ለመፍታት እያከናወነች ያለውን ሥራ በማስተዋወቅ ረገድ በትኩረት እንሰራለን ሲሉ አምባሳደሮቹ አረጋግጠዋል።