ቀጥታ፡

የአደጋ ቅድመ ማስጠንቀቂያና ፈጣን ምላሽ አሰጣጥ ፍኖተ ካርታ ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 18/2015 የአደጋ ቅድመ ማስጠንቀቂያና ፈጣን ምላሽ አሰጣጥ ፍኖተ ካርታ ይፋ ተደረገ።

የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን በፍኖተ ካርታው ላይ ትኩረት ያደረገ አውደ ጥናት እያካሄደ ነው።

ፍኖተ ካርታው ለሚቀጥሉት ስምንት አመታት የሚተገበር ሲሆን አደጋን አስቀድሞ መከላከል ላይ ተቋማት ተቀናጅተው እንዲሰሩ የሚያደርግ መሆኑ ተገልጿል።

ፍኖተ ካርታው ውጤታማ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስርአት መዘርጋት፣ የአደጋ ስጋቶችን መከታተል፣ መተንተን፣ መተንበይ እና በቴክኖሎጂ የተደገፉ ስራዎችን መከወንን ያካተተ ስለመሆኑም ተመላክቷል። 

በክትትል የሚገኘውን መረጃ ተደራሽ ማድረግ፣ ማንቃት እና ተግባራዊ እርምጃ እንዲወሰድ በማድረግ በኩል ፍኖተ ካርታው ቁልፍ ሚና ይጫወታል ተብሏል።

የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ዶክተር ሽፈራሁ ተክማሪያም እንዳሉት ለአደጋ  የማይበገር ማህበረሰብ ለመፍጠር ግብ ተይዞ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ፍኖተ ካርታው ከስራዎቹ መካከል አንዱ መሆኑን ጠቁመው ተቋማት በተናበበ መልኩ እንዲሰሩ የሚያደርግ መሆኑንም ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ድርቅ፣ ጎርፍ እና ግጭቶችን ጨምሮ የተለያዩ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች  እየተከሰቱ መሆኑን ጠቅሰው ላዛ የሚመጥን  ምላሽ አሰጣጥ ስርዓት ሊኖር እንደሚገባ አንስተዋል።

ፍኖተ ካርታው ውጤታማ እንዲሆን ባለደርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባም ኮሚሽነሩ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

በአውደ ጥናቱ ላይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት እየተሳተፉ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም