በህገ-ወጥ መንገድ የተሰበሰበ ከ20 ሚሊየን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ታገደ - ኢዜአ አማርኛ
በህገ-ወጥ መንገድ የተሰበሰበ ከ20 ሚሊየን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ታገደ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 17/2015 በህገ-ወጥ መንገድ የተሰበሰበ ከ20 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ መታገዱን የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት አስታወቀ።
በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በአገር ውስጥ ባንኮች የውጭ አገራት ገንዘብ የሂሳብ ደብተር የሚከፍቱበትን የዳያስፖራ አካውንት ህግና አሠራር የጣሱ የተለያዩ ግለሰቦች በህገ-ወጥ ተግባር ላይ ተሰማርተው መገኘታቸውን የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ለኢዜአ በላከው መግለጫ አመላክቷል።
እስከ አሁን ድረስ በተደረገው ክትትልና ማጣራትም 85 ግለሰቦች የተሳተፉበትና መጠኑ 20 ሚሊዮን 226 ሺህ 583 ዶላር የውጭ አገር ገንዘብ በባንክ እንዲታገድ በማድረግ ለወንጀል ምርመራ መተላለፉን ገልጿል።
ከሃገር ውስጥ ሳይወጡ ውጭ ሃገር ሔደው የተመለሱ በማስመሰል ሃሰተኛ ዴክለራሲዮን ማቅረብ፣ እንዲሁም ከውጭ አነስተኛ የውጭ ምንዛሪ ይዘው በመግባትና ከፍተኛ ገንዘብ ይዘው የገቡ በማስመሰል ቀሪውን በህገወጥ መንገድ መሰብሰብ ለወንጀሉ በማጭበርበሪያ ስልትነት መጠቀማቸውን በመግለጫው ጠቁሟል።
በተጨማሪም የሌላውን ዲክለራሲዮን የራሳቸው በማስመሰል ከሚፈቀደው ውጭ በተለያዩ ባንኮች የዲያስፖራ አካውንት መክፈትና ሌሎች ሃሰተኛ ዲክለራሲዮኖችን ለወንጀል ተግባር ስለመዋላቸው የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ባደረገው ክትትል ማረጋገጡን ገልጿል።
ግለሰቦቹ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የዲያስፖራ አካውንትን በሚመለከት የወጣውን መመሪያ በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 780/2005 ጨምሮ የወንጀል ህግን መተላለፋቸውን በመግለጫው ጠቁሟል።
በመሆኑም የወንጀሉ ተሳታፊዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ ጉዳዩ ለወንጀል ምርመራ መተላለፉን አገልግሎቱ ጠቅሶ መሰል ወንጀሎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የሚያደርገውን ክትትል አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።
በቀጥታም ሆነ በተዘዋወሪ በመሰል ወንጀሎች ላይ ተሳትፎ ያላቸው አካላት የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ከህግ ተጠያቂነት እንደማያመልጡ በመገንዘብ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡም በመግለጫው አሳስቧል።