ቀጥታ፡

በዘመናዊነት ስም ወደ ሀገር የገቡ ጎጂ ልማዶችን በማስወገድ አኩሪ ባህሎቻችንን ማጎልበት ይገባናል - የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር

ሐረር (ኢዜአ) ታህሳስ 17 ቀን 2015 በዘመናዊነት ስም ወደ ሀገር የገቡ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን በአንድነት በማስወገድ አኩሪ ባህሎቻችንን ማጎልበት ይገባናል ሲሉ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ወርቅነሽ ብሩ ተናገሩ።

ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን በመከላከል የማህበረሰቡን ጉዳት ለመቀነስ በሚቻልበት ዙሪያ የተዘጋጀ  ሀገር አቀፍ የንቅናቄ መድረክ ዛሬ በሐረር ከተማ በተካሄደበት ወቅት ሚኒስትር ዴኤታዋ ባደረጉት ንግግር፤ ኢትዮጵያ የብዝሃ ባህል፤ የረጅም ዘመናት ታሪክና የነፃነት ተምሳሌት ሃገር መሆኗን አውስተዋል።

ሀገራችን አንድ የሚያደርጉና የሚያቀራርቡ የበርካታ  ባህሎች ባለቤት ብትሆንም በዘመናዊነት ስም ወደ ሀገር የገቡ አሉታዊ መጤ ልማዶች በህዝቡ አንድነት ብሎም በስራ ባህል ላይ ከፍተኛ ትፅዕኖ ማሳደራቸውን ገልጸዋል፡፡

በህዝብ መካከልም ለዘመናት የቆየውን የአንድነትና የመተባበር ባህል ወደ ፊት በማምጣት ብሎም የስራ ባህልን በማጎልበት ሀገራችን የተቸረችውን የተፈጥሮ ሃብቶች በማልማት መጠቀም ይገባናል ብለዋል፡፡

ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ ህዝቡን ወደ ኋላ እየጎተቱ የሚገኙ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን በማስወገድ አንድነትን የሚያጠናክሩ ባህሎችን ማጎልበት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ የበርካታ አኩሪ ባህሎች  ባለቤት ብትሆንም አሉታዊ መጤ ልማዶች በስልጣኔ ሰም ገብተው መስፋፋታቸው በሀገሪቱ ባህላዊ እሴቶች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ በመፍጠር ችግር መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የሐረሪ ክልል ባህል ቅርስ እና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ አቶ ተወለዳ አብዶሽ ናቸው፡፡

በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ስነ-ልቦና ላይ ችግር በመሆናቸው የሚመለከታቸው አካላት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ሊንቀሳቀሱ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

በሃረማያ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህርና ተመራማሪ ዶክተር መሃመድ ሃሰን በበኩላቸው፤ መጤ የሆኑ ጎጂ ልማዶች ሀገሪቱን አደጋ ላይ እየጣሉ ናቸው ብለዋል ፡፡

በተለይ የስራ ባህላችንን በማዳከሙ  ምርትና ምርታማነት ላይ ጫናው ከፍተኛ በመሆኑ አምራች የሆነውን ወጣቱን ክፍል በንቅናቄው በማሳተፍ ችግሩን ለማቃለል ሊሰራ ይገባል ነው ያሉት፡፡

ማህበረሰቡ አሉታዊ የሆኑ መጤ ጎጂ ልማዶችን በመተው ቀድሞ የነበሩ የቁጠባ ብሎም አንድነትና መተባበርን የሚያጎለብቱ ባህላዊ እሴቶችን የመጠበቅ ማህበራዊ ሃላፊነቱን እንዲወጣ በንቅናቄው መድረክ ላይ መልዕክት ተላልፏል።

"የባህል ፀጋዎቻችንን በማጎልበት ትውልድን እንገንባ" በሚል መሪ ሀሳብ በሐረር የተካሄደው የንቅናቄ መድረክ በሌሎችም የሀገሪቱ  ከተሞች እንደሚቀጥል ተመልክቷል።

የንቅናቄ መድረክ ያዘጋጁት የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር፤ የሴቶችና ማህበራዊ  ጉዳይ ሚኒስቴር፤ የሐረማያ ዩኒቨርሲቲና የሐረሪ ክልል ባህል ቅርስ እና ቱሪዝም ቢሮ በመተባባር እንደሆነ በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም