ኢትዮ-ቴሌኮም በትግራይ ክልል በ27 ከተሞች ዳግም አገልግሎት መጀመሩን አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮ-ቴሌኮም በትግራይ ክልል በ27 ከተሞች ዳግም አገልግሎት መጀመሩን አስታወቀ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 17/2015 ኢትዮ ቴሌኮም በትግራይ ክልል በ27 ከተሞች ዳግም አገልግሎት መጀመሩን የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ ገልፀዋል።
ሌሎች የፌደራል መንግሥት መሠረታዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትም አገልግሎቶቻቸውን በተሟላ መልኩ ለማስቀጠል እየሠሩ መሆኑን አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በበኩሉ የትግራይ ክልል ሙሉ ለሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ ከብሔራዊ የኃይል ቋት ጋር መገናኘቱን ተናግረዋል፡፡
የመንግሥት መሠረታዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አመራሮች በመቀሌ ከተማ ከህብረተሰቡ ተወካዮች ጋር ውይይት አድርገዋል።
በመድረኩም የህብረተሰቡ ተወካዮች የባንክ ፣ የቴሌኮምና የንግድ አገልግሎቶች በስፋት እና በፍጥነት እንዲጀመሩላቸው ጠይቀዋል።
በውይይቱ ማብራሪያ የሰጡት የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ፤ በጦርነቱ በርካታ የቴሌኮም መሠረተልማት መውደሙን ጠቅሰው፥ በዚህም ከ1 ሺህ 800 ኪሎ ሜትር የማያንስ የፋይበር ኦፕቲክ መስመር ጥገና እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
እስካሁን ባለው ሂደት 931 ኪሎሜትር የሚሆነውን መጠገን መቻሉን ተናግረዋል፡፡
በዚህም 27 ከተሞች ዳግም አገልግሎት ማግኘት ችለዋል ነው ያሉት፡፡
ከባንክና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ባሻገር ኢንተርፕራይዞችና የሰብዓዊ እርዳታ ድርጅቶች የቴሌኮም አገልግሎት እንዲያገኙ በቁርጠኝነት እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
መቀሌን ጨምሮ በስድስት አቅጣጫ የጥገና ቡድን ተሰማርቶ እየሠራ ሲሆን በቅርቡ የቴሌኮም አገልግሎት ያልተጀመረባቸው አካባቢዎች አገልግሎቱን እንደሚያገኙ ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ ሰለሞን ጣሰው በበኩላቸው የትግራይ ክልል ሙሉ ለሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ ከብሔራዊ የኃይል ቋት ጋር መገናኘቱን ተናግረዋል፡፡
በዚህም በርካታ ከተሞች የኤሌክትሪክ አገልግሎት ማግኘት ጀምረዋል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ በተወሰኑ ከተሞች የባንክ አገልግሎት መጀመሩን ገልጸው፤ መቀሌን ጨምሮ በትላልቅ ከተሞች የባንክ ግብይት ኦዲት እንደተጠናቀቀ በአፋጣኝ መደበኛ የባንክ አገልግሎት እንደሚጀመር አረጋግጠዋል።
ለዚህም ቅርንጫፎች ያሉበትን ሁኔታና የኦዲት ስራዎችን የሚያሳልጥ የባለሙያዎች ቡድን መቀሌ ገብቶ ሥራ መጀመሩን ጠቅሰዋል።
የኢትየጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው፥ የሽሬ አውሮፕላን ማረፊያ ለመደበኛ በረራ አገልግሎት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።
የመቀሌና የአክሱም ኤርፖርቶችም የመብራትና የቴሌኮም አገልግሎቶችን እንዳገኙ መደበኛ በረራ ለመጀመር ዝግጀት እየተደረገ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡