ቀጥታ፡

ብሔራዊ የቦክስ ክለቦች ሻምፒዮና ታህሳስ 20 በአዲስ አበባ ይጀመራል

አዲስ አበባ(ኢዜአ) ታህሳስ 17/2015 የ2015 ዓ.ም የመጀመሪያ ዙር ብሔራዊ የክለቦች ሻምፒዮና በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ታህሳስ 20 ቀን 2015 ይጀመራል።

ለአራት ቀናት በሚቆየው ሻምፒዮና በወንዶች 90 እንዲሁም በሴቶች 30 በድምሩ 120 ተወዳዳሪዎች ይሳተፋሉ።

አዲስ አበባ ፖሊስ፣ፌደራል ፖሊስ፣ፌደራል ማረሚያ ቤቶች፣ድሬዳዋ ከተማ፣የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ፣ደሴ ከተማ፣ፋሲል ከነማ እና ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የውድድሩ ተሳታፊ ክለቦች ናቸው።

በወንዶች ከ48 እስከ ከ92 ኪሎ ግራም በላይ(91 ፕላስ)፤ በሴቶች ከ48 እስከ 63 ኪሎ ግራም ውድድሩ የሚካሄድባቸው የክብደት ዘርፎች ናቸው።

ሻምፒዮናው የቦክስ ክለቦች የውድድር አማራጭ የመፍጠር አላማ እንዳለው የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።

በግንቦት ወር 2015 ዓ.ም በሕንድ አስተናጋጅነት በሚካሄደው ዓለም አቀፍ የሴቶች የቦክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያን ወክለው የሚሳተፉ ተወዳዳሪዎች ለመምረጥ እንደሚያግዝም ገልጿል።

ውድድሩን በዓመት አራት ጊዜ የሚካሄድ በመሆኑ ለቦክስ ክለቦች የውድድር አማራጭን እንደሚያሰፋ ተነግሯል።

ዓመቱ ውስጥ የሚካሄዱ ቀሪ ሶስት ውድድሮች በጎንደር፣ አርባ ምንጭ እና አዲስ አበባ ከተሞች ለማከናወን መታሰቡን ፌዴሬሽኑ አመልክቷል።

በአራቱ ከተሞች የሚካሄዱት ውድድሮች አጠቃላይ ውጤት ተደምሮ በሁለቱም ጾታዎች አጠቃላይ አሸናፊ ክለቦች እንደሚለዩም አስታውቋል።

አዲስ አበባ ፖሊስ በሁለቱም ጾታዎች የ2014 ዓ.ም ብሔራዊ የቦክስ ክለቦች ሻምፒዮና አጠቃላይ አሸናፊ እንደነበር የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም