ቀጥታ፡

መንግሥት ለአካል ጉዳተኞች አጋዥ የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እንዲሰራ ተጠየቀ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታኅሳስ 17/2015 መንግሥት አካል ጉዳተኞች በልማት ላይ ያላቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ የሚረዱ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት መሥራት እንዳለበት የኢትዮጵያ ሴንተር ፎር ዲሴቢሊቲ ኤንድ ዴቨሎፕመንት ገለጸ።

የኢትዮጵያ ሴንተር ፎር ዲሴቢሊቲ ኤንድ ዴቨሎፕመንት ”አካታች የፈጠራ ሥራና ሽግግራዊ መፍትሄ ለኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ሁለንተናዊ ተደራሽነት” በሚል መሪ ሃሳብ የአካል ጉዳተኞችን ቀን አክብሯል።

ቀኑ በኢትዮጵያ ለ30ኛ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ31ኛ ጊዜ የተከበረ ሲሆን በመድረኩ የቴክኖሎጂ ፈጠራና ተደራሽነት በአካል ጉዳተኞች ላይ የሚል ይዘት ያለው የመወያያ ፅሁፍ ቀርቦ ምክክር ተካሂዶበታል።

የኢትዮጵያ ሴንተር ፎር ዲሴቢሊቲ ኤንድ ዴቨሎፕመንት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታሁን ስምኦን በርካታ አካል ጉዳተኞች ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ የሚያስችሏቸውን የቴክኖሎጂ ውጤቶች ማግኘት እንዳልቻሉ ተናግረዋል።

መንግሥትን ጨምሮ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በቴክኖሎጂ ተደራሽነትና ጠቀሜታ ላይ ያላቸው ግንዛቤ በሚፈለገው ልክ አለማደግ እንደ ምክንያት ተጠቃሽ መሆኑን ነው የገለጹት።

እንደ አገር የተለያዩ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመጠቀም የአካል ጉዳተኞችን ሕይወት መቀየር ይቻላል ብሎ ያለማመን ሁኔታዎች እንደሚስተዋሉም አክለዋል።

አካል ጉዳተኞች ያለባቸው ጉዳት ሳይገድባቸው በልማት ላይ ያላቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ የሚያግዙ አጋዥ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ተደራሽ በማድረግ ረገድ መንግስት በትኩረት ሊሰራ ይገባልም ሲሉ ገልፀዋል፡፡

የአካል ጉዳተኞችን የቴክኖሎጂ ተደራሽነት ለማሳደግ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተሳትፎን የሚጠይቅ በመሆኑ በጋራ ልንሰራ ይገባል ሲሉ ጥሪ አቅበዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች አካል ጉዳተኞች ያለባቸው የጉዳት አይነት ሳይገድባቸው ሥራቸውን የበለጠ ቀልጣፋና ውጤታማ ለማድረግ የሚያግዟቸውን የቴክኖሎጂ ውጤቶች በስፋት ተደራሽ ለማድረግ ሁሉም አካላት በእኔነት ስሜት እንዲሰራ ጠይቀዋል።

መንግሥት አካል ጉዳተኞች ሊጠቀሙባቸው የሚችሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በማዘመን እንዲሁም አዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ወደ አገር ውስጥ በማስገባት የአካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚኒት ሊያሳድግ ይገባልም ሲሉ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም