ቀጥታ፡

የመጀመሪያዋ የመሬት ምልከታ ሳተላይት የመጠቀችበት ሦስተኛ ዓመትና የጂኦግራፊክ ኢንፎርሜሽን ቀን በአዲስ አበባ ተከበረ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 17 ቀን 2015 የመጀመሪያዋ የመሬት ምልከታ ሳተላይት የመጠቀችበት ሦስተኛ ዓመትና የጂኦግራፊክ ኢንፎርሜሽን ቀን በአዲስ አበባ ተከበረ።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዲኤታ ሁሪያ አሊ ዲጂታል ቴክኖሎጂን በመጠቀም የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለማሳደግ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነቷን ለማሳደግ በትኩረት እየሰራች መሆኑንም አክለዋል።

የመጀመሪያዋ የመሬት ምልከታ ሳተላይት መምጠቋ ለኢኮኖሚው ዘርፍ ካላት ጠቀሜታ ጎን ለጎን የአገር ገፅታ ግንባታውም ትልቅ አስተዋጽዖ አድርጋለች ብለዋል።

መንግሥት ለዘርፉ ከሰጠው ትኩረት አኳያ አሁን ላይ የግሉ ዘርፍ በመሬት መረጃ አሰባሰብ የቴክኖሎጂ ሥራዎች ላይ ተሳትፏቸው እያደገ መምጣቱን ጠቁመዋል።  

ባለፉት ሶስት አመታት በዘርፉ የታዩ ሥራዎች አገሪቱ ዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን ለመጠቀም ወይንም የ2025 የዘርፉን እቅድ ለማስፈፀም ትልቅ ግብዓት ይሆናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጂኦ-ስፓሻል ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዲሳ ይልማ በበኩላቸው ከሳተላይት፤ ከአውሮፕላን ላይ ከሚገጠሙ ካሜራዎች፤ በመሬት ላይ ከሚከናወኑ ሳተላይቶችና ከቅየሳ መሳሪዎች መረጃ እየተሰበሰበ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

በዚህም አገሪቱ በግብርና ሥራ፣ ለከተማ ልማት፣ ለመንገድ ሥራ፣ ለመሬት እና ውሃ ኃብት አስተዳደር፣ ለደን ሽፋንና ለቱሪዝም አገልግሎት ጥቅም ላይ እየዋሉ መሆኑን አብራርተዋል።   

ለኅብረተሰቡ አሰራሮችን ከማዘመንና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኝ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን የማልማት ሥራ መከናወኑን ተናግረዋል።

ለአብነትም በቅርቡ ከቱሪዝም ሚኒስትር ጋር በመተባበር የተሰራው የቪዚት ኢትጵዮጵያና በአርባ ምንጭ ከተማ ተመርቆ ወደ ሥራ የሚገባው የቱሪስት ሳይት የመሬት መረጃ ቴክኖሎጂ ተጠቃሽ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም