የመንገድ ትራፊክ አደጋ ማሻሻያ ረቂቅ ደንብ ላይ ውይይት እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የመንገድ ትራፊክ አደጋ ማሻሻያ ረቂቅ ደንብ ላይ ውይይት እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 17/2015 የመንገድ ደኅንነትና መድን ፈንድ አገልግሎት የመንገድ ትራፊክ አደጋ ለመቀነስ የተዘጋጀ የመንገድ ትራፊክ አደጋ ማሻሻያ ረቂቅ ደንብ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተወያየ ነው።
የማሻሻያ ረቂቅ ደንቡ የመንገድ ትራፊክ አደጋዎችን ለመከላከልና የተሸከርካሪ አደጋ ተጎጂዎችን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመቀነስ ታሳቢ ያደረገ ነው ተብሏል።
የመንገድ ደህንነትና መድን ፈንድ የሕግ አማካሪና ጠበቃ አቶ ይታያል መኮንን የትራፊክ አደጋ መተኪያ የሌለው የሰው ህይወት እየነጠቀና ከቀላል እስከ ከባድ አካል ጉዳት እያደረሰ ነው።
በኢትዮጵያ በ2014 ዓ.ም ብቻ በደረሰ የትራፊክ አደጋ ከ13 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት የንብረት ጉዳት እንደደረሰ አገልግሎቱ ለማሳያነት አቅርቧል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመንገድ የትራፊክ አደጋዎች ምክንያት በሰው ላይ የሚደርሰው ሞትና ከባድ ጉዳት መጠነኛ መሻሻል ማሳየቱን ገልጸዋል።
በ2014 ዓ.ም በንብረት ላይ የደረሰው ጉዳት በመንገድ የትራፊክ አደጋዎች ምክንያት እየደረሰ ያለው አደጋ መጨመሩን የሚያሳይ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ይህም በዋናነት ከፍጥነት በላይ በማሽከርከር ጠጥቶ በመንዳት እና በሌሎች ምክንያቶች የትራፊክ አደጋ ችግሮች እየተከሰቱ መሆኑን አመላክተዋል።
በመንገድ ትራፊክ አደጋ ከ2005 እስከ 2014 ዓ.ም ባለው ጊዜ ደግሞ ከ30 ቢሊዮን ብር በላይ ንብረት መውደሙም ተገልጿል።
ረቂቅ ደንቡ ወደ ሥራ ሲገባ እነዚህን አደጋዎች ለመቀነስ የራሱ ሚና እንደሚኖረው ታምኖበታል።