የቱሪዝም ሀብቱን በማስተዋወቅ ረገድ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩበት እንደሚገባ ተመላከተ - ኢዜአ አማርኛ
የቱሪዝም ሀብቱን በማስተዋወቅ ረገድ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩበት እንደሚገባ ተመላከተ
ታህሳስ 17/2015 (ኢዜአ ) በኢትዮጵያ ያሉ እምቅ የቱሪዝም ሀብቶችን ማስተዋወቅ ላይ መገናኛ ብዙሃንና ባለሙያዎች ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩበት እንደሚገባ ተመላከተ።
የጌዲኦ ተፈጥሯዊና ባህላዊ መልከዓ ምድር ቅርስን ከተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የተውጣጡ ባለሙያዎች ጎብኝተዋል።
የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ባሰናዳው የጉብኝት መርሃ ግብር ላይ የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌውን ጨምሮ ከክልልና ዞን የተወከሉ ተሳትፈዋል።
የጌዲኦ መልከዓ ምድር ቅርስ በውስጡ ጥብቅ ደን፣ ጥምር ግብርናና ረጅም ዓመታትን ያስቆጠሩ ትክል ድንጋዮችን በውስጡ ያካተተ ሲሆን በምስራቅ አፍሪካ በእድሜ ረጅም እንደሆኑ የተነገረላቸው ከ6000 በላይ የትክል ድንጋዮች እንደሚገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ።
ቅርሱን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንሰና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ እየተሰራ ነው።
የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ህይወት ኃይሉ እንደተናገሩት፤ የጌዲኦ ባህላዊ መልከዓ ምድር ቅርስ የቀደሙ አባቶች አገር በቀል እውቀታቸውን ተጠቅመው ትውልድ እንዲማርበት ጠብቀው አቆይተዋል።
ኢትዮጵያ የሥልጣኔ መገለጫ መሆኗን ከሚያሳዩ ቅርሶች መካከል አንዱ የጌዲኦ መልከዓ ምድር ቅርስ መሆኑን አንስተው በአሁኑ ወቅት ቅርሱ ለጥናትና ምርምር አድራጊዎችም ትልቅ ግብዓት መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም በመልከዓ ምድሩ ውስጥ ያለው ጥብቅ ደን በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ዘርፍ አርአያ የሚሆን ነው ሲሉም አክለዋል።
እንደ ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ ገለጻ በጌዲኦ ገዳ ሥርዓት አንድ ዛፍ የሚቆርጥ ሰው ሁለት ችግኝ መትከል እንዳለበት ሥርዓቱ እንደሚያስገድድ ገልጸው በመልከዓ ምድሩ ውስጥ ደኑ ተጠብቆ ለትውልድ መተላለፉ ትልቁን ሚና ተጫውቷል።
መገናኛ ብዙሃን መሰል ተሞክሮዎች ወደ ሌሎች አካባቢዎች እንዲሰፉ የድርሻቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።
በጉብኝቱ ላይ ከተሳተፉት መካከል የማውንቴንስ ሚዲያ መስራች ጋዜጠኛ አስቻለው ጌታቸው ለኢዜአ እንዳለው፤ በመልከዓ ምድር ውስጥ ማኅበረሰቡ ከተፈጥሮ ጋር ባለው መስተጋብር የሚጠቀመው ጥበብ ለሌሎች አካባቢዎች አርአያ የሚሆን ነው።
እንደዚህ ዓይነት ማኅበረሰቡን ገላጭ የሆኑ አገር በቀል እውቀቶች መገናኛ ብዙሃን በአግባቡ እንዲያስተዋውቁ ሊሰራ ይገባል ብሏል።
ኢትዮጵያ ያሏት የቱሪዝም ኃብቶች ላይ መገናኛ ብዙሃን አጀንዳ ቀርጸው በትኩረት ሊሰሩበት ይገባል ሲልም ነው ጋዜጠኛ አስቻለው አጽንኦት የሰጠው።
ሌላዋ ጎብኚ የአዋሽ ኤፍ ኤም ሬዲኦ ጋዜጠኛ ዓለምነሽ ኩምሳ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በቱሪዝም ዘርፍ ያላቸውን አቅም ማጎልበት ይገባቸዋል ብላለች።
በዘርፉ የሚመለከታቸው አካላት መሰል የጉብኝት መርሃ ግብሮችን በማዘጋጀት ጋዜጠኛው በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው ሊሰሩ እንደሚገባና ቀጣዩ ትውልድ ስለአገሩ እውቀት እንዲኖረው የሚያደርጉ ስራዎች በመገናኛ ብዙሃን በኩል ሊሰራ ይገባል ነው ያለችው።
የሀገረሰብ ሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅ ጋዜጠኛ አስናቀ ብርሃኑ የጌዲኦ መልከዓ ምድር ቅርስን የበለጠ በማስተዋወቅ የአገር ውስጥም የውጭም ጎብኚዎች በስፋት እንዲጎበኙት መስራት ይጠይቃል ብሏል።
ጋዜጠኞቹ የጌዲኦ ተፈጥሯዊና ባህላዊ መልከዓ ምድር ቅርስን ለማስተዋወቅ የበኩላቸውን እንደሚወጡም አረጋግጠዋል።