ኤሌክትሪክ ተቋርጦባቸው የነበሩ 80 ከተሞች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ሆኑ - ኢዜአ አማርኛ
ኤሌክትሪክ ተቋርጦባቸው የነበሩ 80 ከተሞች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ሆኑ
ታህሳስ 17/2015 (ኢዜአ) በሰሜን ኢትዮጵያ በነበረው ግጭት በደረሰ የኤሌክትሪክ መሠረተ-ልማት ውድመት ኤሌክትሪክ ተቋርጦባቸው የነበሩ 80 ከተሞች የአገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ኤሌትሪክ አገልግሎት ገለጸ።
በግጭቱ ምክንያት ኤሌክትሪክ ተቋረጠባቸው የነበሩ የትግራይ፣ አማራና አፋር ክልል አካባቢዎችን ዳግም የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ በተደረገ ከፍተኛ ጥረት 80 ከተሞች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆናቸው ተጠቅሷል።
ቀሪ 27 ከተሞችን መልሶ ለማገናኘት የጥገና ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝም ነው የተገለጸው።
ተቋሙ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በተከሰተው ጦርነት በኤሌክትሪክ ማሰራጫ መሰረተ ልማቶች ላይ የደረሰውን ጉዳት ከስር ከስር መልሶ በመጠገን የኤሌክትሪክ አገልግሎት የተቋረጠባቸውን አካባቢዎች ዳግም ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ እንደሚገኝ ተመላክቷል።