ቀጥታ፡

የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ከዓለም ዋንጫ በኋላ በ‘ቦክሲንግ ዴይ’ ጨዋታዎች ዛሬ ይመለሳል

አዲስ አበባ(ኢዜአ) ታህሳስ 17/2015 በ22ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ምከንያት ለአንድ ወር ተቋርጦ የነበረው የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ በሚደረጉ የ‘ቦክሲንግ ዴይ’ ጨዋታዎች ይጀመራል።

በዓለም ዋንጫው ጭር ብለው የነበሩት የፕሪሚየር ሊግ ክለብ ስታዲየሞች በሺዎች በሚቆጠሩ ደጋፊዎች በድጋሚ ይሞላሉ።

በ37 ነጥብ ፕሪሚየር ሊጉን አርሰናል በኤምሬትስ ከምሽቱ 5 ሰአት ከዌስትሃም ዩናይትት ጋር ይጫወታል።

ማይክል አርቴታ በዓለም ዋንጫው ጉዳት ያጋጠመውን የአጥቂያቸውን ጋብርኤል ጄሱስ ግልጋሎት አያገኙም።

በቪላ ፓርክ ከምሽቱ 2 ሰአት ከ30 አስቶንቪላ ከሊቨርፑል ይጫወታሉ።

በጂቴክ ኮምዩኒቲ ስታዲየም ከቀኑ 9 ሰአት ከ30 ብሬንትፎርድ ከቶተንሃም ሆትስፐርስ የ‘ቦክሲንግ ደይ’ የመክፈቻ ጨዋታ ያደርጋሉ።

ክሪስታል ፓላስ ከፉልሃም፣ኤቨርተን ከዎልቨርሀምፕተን ወንድረርስ፣ ሌይስተር ሲቲ በሊጉ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ኒውካስትል ዩናይትድ እና ሳውዝሀምፕተን ከብራይተን ኤንድ ሆቭ አልቢዮን በተመሳሳይ ከምሽቱ 12 ሰአት ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ነገ በስታምፎረድ ብሪጅ ቼልሲ ከቦርንማውዝ ከምሽቱ 2 ሰአት ከ30 እንዲሁም በኦልትራፎርድ ማንቸስተር ዩናይትድ ከኖቲነግሃም ፎረስት ከምሽቱ 5 ሰአት ይጫወታሉ።

በ32 ነጥብ በሊጉ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ማንችስተር ሲቲ ከነገ በስቲያ ወደ ኢላንድ ሮድ ስታዲየም በማቅናት ከምሽቱ 5 ሰአት ከሊድስ ዩናይትድ ጋር ጨዋታውን የሚያደርግ ይሆናል።

የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነትን የማንቸስተር ሲቲው አርሊንግ ሃላንድ በ18 ግቦች ይመራል።

የቶተንሃም ሆትስፐርሱ ሃሪ ኬን በ12 እንዲሁም የብሬንትፎርዱ ኢቫን ቶኔይ በ10 ግቦች ይከተላሉ።

‘ቦክሲንግ ደይ’ የፈረንጆች ገና በተከበረ በቀጣዩ ቀን ያለው ስያሜ ነው።በገና ወቅት በርካቶች ስጦታ የሚሰጣጡት በሳጥን (Box) መሆኑን ተከትሎ በዛን ወቅት የሚደረጉ ጨዋታዎችም ቦክሲንግ ደይ ተብለው ተሰይመዋል።

‘ቦክሲንግ ደይ’ በዩናይትድ ኪንግደም የሚኖሩ ዜጎች የበጎ አድራጎት እና መልካም ተግባር የሚከውኑበት ዕለት ነው።

ክለቦች በቦክሲንግ ደይ ጨዋታዎች የትኬት ዋጋ ላይ ከፍተኛ ቅናሽ በማድረግ በተለይ ሕጻናት ስታዲየም እንዲገቡ ያመቻቻሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም