የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለአፍሪካ እግር ኳስ ሻምፒዮና ያለፈበት ጉዞ ምን ይመስላል? - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለአፍሪካ እግር ኳስ ሻምፒዮና ያለፈበት ጉዞ ምን ይመስላል?


አዲስ አበባ(ኢዜአ) ታህሳስ 17/2015 ሰባተኛው የአፍሪካ አገራት እግር ኳስ ሻምፒዮና ከጥር 5 እስከ 25 ቀን 2015 ዓ.ም በአልጄሪያ አስተናጋጅነት ይካሄዳል።
በአገር ውስጥ ሊግ ብቻ የሚሳተፉ ተጫዋቾች ብቻ በሚሳተፉበት ውድድር ኢትዮጵያን ጨምሮ 18 አገራት ይካፈላሉ።
ዋልያዎቹ በምድብ አንድ ከአስተናጋጇ አልጄርያ፣ሞዛምቢክ እና ሊቢያ ጋር ተደልድለዋል።
ለመሆኑ በውበቱ አባተ የሚሰለጥነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የአልጄሪያ የቻን ተሳትፎ የማጣሪያ ጉዞ ምን ይመስላል?
ዋልያዎቹ በቻን ቅድመ ማጣሪያ የተገናኙት ከደቡብ ሱዳን ብሔራዊ ቡድን ጋር ነበር።
በታንዛንያ 60 ሺህ ተመልካች በሚያስተናግደው ቤንጃሚን ምካፓ ስታዲየም ሐምሌ 15 ቀን 2015 ዓ.ም በተደረገው የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ ያለ ምንም ግብ በአቻ ውጤት ተጠናቀቀ።
ብሔራዊ ቡድኑ ሐምሌ 21 ቀን 2015 ዓ.ም በድጋሚ በቤንጃሚን ምካፓ ስታዲየም በተደረገው የመልስ ጨዋታ ደቡብ ሱዳንን 5 ለ 0 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት አሸነፈ።

አማኑኤል ገብረሚካኤል፣ይገዙ ቦጋለ፣መስዑድ መሐመድ፣ረመዳን የሱፍ እና ፒተር ሜከር በራሱ ግብ ላይ ለዋልያዎቹ ግቦቹን አስቆጥረዋል።
ውጤቱንም ተከትሎ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በደርሶ መልስ ውጤት 5 ለ 0 በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር አለፈ።
ብሔራዊ ቡድኑ በሁለተኛ እና የመጨረሻ የማጣሪያ ዙር የተገናኘው ከርዋንዳ አቻው ጋር ነበር።
ዋልያዎቹ ነሐሴ 20 ቀን 2015 ዓ.ም በቤንጃሚን ምካፓ ስታዲየም ባደረጉት ጨዋታ ያለ ምንም ግብ አቻ ተለያዩ።
ነሐሴ 28 ቀን 2015 ዓ.ም 10 ሺህ ተመልካች በሚያስተናግደው ሁዬ ስታዲየም በተደረገው የመልስ ጨዋታ ዳዋ ሆቴሳ በ22ኛው ደቂቃ በቅጣት ምት ባስቆጠራት አስደናቂ ግብ ኢትዮጵያ ርዋንዳን 1 ለ 0 አሸነፈች።
ውጤቱንም ተከትሎ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአልጄሪያው የቻን እግር ኳስ ውድድር ማለፉን አረጋገጠ።
በምድብ አንድ የሚገኙት ዋልያዎቹ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ጥር 5 ቀን 2015 ዓ.ም ከሞዛምቢክ ጋር ያደርጋሉ።
ጥር 9 ቀን 2015 ዓ.ም ከአስተናጋጇ አገር አልጄሪያ እንዲሁም ጥር 13 ቀን 2015 ዓ.ም ከሊቢያ ይጫወታሉ።
የዋልያዎቹ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ታህሳስ 14 ቀን 2015 ዓ.ም በአልጄሪያ አስተጋጅነት ለሚካሄደው የአፍሪካ እግር ኳስ ሻምፒዮና(ቻን) ዝግጅት ለ28 ተጫዋቾች ጥሪ ማድረጋቸው ይታወቃል።

አሰልጣኙ ከዚህ ቀደም ለቻን ውድድር ቅድመ ዝግጅት 42 ተጫዋቾችን ያካተተ ጊዜያዊ የተጫዋቾች ጥሪ አድርገው ነበር።
በድሬዳዋ እየተካሄደ በሚገኘው ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድር ላይ ተገኝተው የተጫዋቾችን ወቅታዊ ብቃት እና ሁኔታ በመገምገም የተጫዋቾችን ቁጥር ወደ 28 በመቀነስ ጥሪ ማድረጋቸውን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።
ተጫዋቾቹ ነገ ወሎ ሰፈር በሚገኘው የፌዴሬሽኑ ጽህፈት ቤት በመገኘት ሪፖርት ካደረጉ በኋላ በቀጣዩ ቀን የጤና እና የአካል ብቃት ምርመራ እንደሚደረግላቸው ተነግሯል።
ታህሳስ 19 ቀን 2015 ዓ.ም ተጫዋቾቹ ልምምድ ማድረግ እንደሚጀምሩ ተገልጿል።